በአፋር ክልል የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

80

ሰመራ መጋቢት 18/2011 በአፋር ክልል የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ገለጹ።

በክልሉ ከ32 ወረዳዎች የተወከሉ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የሚመክር የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ እንደገለጹት ኢትዮዽያ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻን በ2025 ለማስቆም የገባችውን ቃል ተፈጻሚ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ነው።

የቁርጠኝነትና የግንዛቤ ማነስ፣ ግርዛትን ሃይማኖታዊ መሰረት እንደለው አድረጎ ማየትና በህግ አስፈጻሚው በኩል በሚታየው ክፍተት  ምክንያት የሴት ልጅ ግርዛት አሁንም በክልሉ አለመቆሙን አመልክተዋል።

ግርዛት በሴቶች ጤና ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት ባልተናነሰ በሀገር ሁለንተናዊ እድገት ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ቀላል አለመሆኑንም ጠቁመዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ መሪዎች በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን  ግርዛት ለማስቀረት በባለቤትነት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም አቶ አወል አሳስበዋል።

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ በበኩላቸው የሴት ልጅ ግርዛት በሴቶችና ታዳጊ ህጻናት ላይ የጤናና የስነልቦና ጉዳት እንደሚያስከትል ገልጸዋል።

ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ባለፉት ዓመታት ለህብረተሰቡ ሲሰጡ ከነበሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች በተጓዳኝ የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ይሁንና በክልሉ አሁንም የሴት ልጅ ግርዛት አለመቆሙን መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ አስረድተዋል።

"የችግሩን አስከፊነት ከግንዛቤ በማስገባት በክልሉ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የሚሰራው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

በሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ማህደር ቢተው በበኩላቸው እንዳሉት በ2016 ይፋ በተደረገው ስነተዋልዶ ጤና መረጃ መሰረት የሴት ልጅ ግርዛት በአፋርና ሱማሌ ክልሎች በስፋት ይከናወናል።

የኢትዮጵያ ስነ-ተዋልዶ ጤና ጥናት በ2016 ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ዓመት ከሆኑ የአፋር ክልል ሴቶች 91 ከመቶ የሚሆኑት ተገርዘዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም