ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የተማሪው ጥረትና የመምህሩ ክትትልና ድጋፍ ወሳኝ መሆናቸውን የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ

1348

አዲስ አበባ  ግንቦት 24/2010 ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ተማሪው በግሉ የሚያደርገው ጥረት እንዲሁም የመምህሩ ክትትልና ድጋፍ ወሳኝ መሆናቸውን የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመማር ማስተማሩ ሂደትና ውጤት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ለኢዜአ አስተያየት የሰጡት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የሚታየው የትምህርት ጥራት አንዱ ክፍተት የመምህራንና የተማሪዎች ቸልተኝነት ነው።

ያም ብቻ ሳይሆን ተግባር ተኮር ትምህርት አሰጣጥና የአጋዥ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማነስም ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ “አገርን ለማሳደግ ካስፈለገ መስራት ያለብን የሰው ልጅ አዕምሮ ላይ ነው” የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ንግግር እውን ለማድረግ የመማር ማስተማር ሂደቱ በሁሉም ደረጃ ሊፈተሽ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከዘንድሮ የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂዎች ጋር ለመወያየት ፕሮግራም መያዛቸው ለሌሎች በትምህርት ላይ ለሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መነቃቃትና ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ከዩኒቨርሲቲዎች በከፍተኛ ማዕረግ የሚመረቁ ተማሪዎች በውጭ አገር ነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ ይሆናሉ’ ማለታቸው ይታወሳል።

ከዛ ባለፈም በቤተ-መንግሥት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በአፍሪካ ኅብረትና በሌሎች ተቋማት ጉብኝትና ውይይትም እንዲያደርጉ ከወዲሁ እንደሚመቻችላቸው ጠቁመው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ለኢዜአ አስተያታቸውን የሰጡ የሰመራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡት ቃል በተማሪዎች ዘንድ ትልቅ መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በከፍተኛ ውጤት የሚመረቁ ተማሪዎች በቤተ-መንግስት ከሚኖራቸው የአንድ ሳምንት ቆይታ በተጨማሪ  ነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚደረግ መናገራቸው ይታወቃል።