በመቀሌ የተደረገልን አቀባበልና መስተንግዶ አስደስቶናል---ተማሪ ስፖርተኞች

56

መቀሌ መጋቢት 18/2011 መቀሌ ላይ የተደረገላቸው አቀባበልና መስተንግዶ እንዳስደሰታቸው የመላው ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር ተሳታፊዎች ገለፁ።

ህዝቡ ያሳያቸው ፍቅርና በክልሉ መንግስትና ተቋማት እየተደረገላቸው ባለው መስተንግዶ ደስተኛ መሆናቸውን ተሳታፊ ተማሪዎች ተናግረዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የአትሌቲክስ ዘርፍ ተወዳዳሪ ተማሪ ጌታነህ ታሪኩ "ስፖርተኞች መቀሌ ስንገባ ህዝቡ እቅፍ አበባ በመያዝ ምግብና ውሃ አዘጋጅቶ ያደረገልን አቀባበል አስደሳች ነበር "ብሏል ።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የመኝታና የምግብ አገልግሎት እንደፈቀደላቸውና የከተማ አውቶቡሶችም ነጻ የትራንስፖርት እገልግሎት እየሰጣቸው መሆኑን ተናግሯል።

"በተዘጋጀልን የማረፊያ ስፍራ የሻይና ቡና አገልግሎት እያገኘን ጊዜያችንን በደስታ እያሳለፍን ነው " ያለችው ደግሞ ከአማራ ክልል በጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ተወዳዳሪ የሆነችው ተማሪ ትርፍነሽ በአምላክ ነች።

ከጋምቤላ ክልል በመምጣት የተሳተፈው ተማሪ ባንቱ ቢገሳ በበኩሉ "የተደረገልን ኢትዮጵያዊ ባህል የተላበሰ አቀባበል እርስ በርስ ፍቅርና አንድነትን የሚያጎለብት ነው" ብሏል ።

ከሐረሪ ክልል የመጣው ተወዳዳሪ ተማሪ ጀማል ጁሀር በበኩሉ "የመቀሌ ህዝብ ፍቅርና ክብር ስለቸረን ውድድራችንን በደስታ እያካሄድን ነው" ብሏል ።

መጋቢት 14 ቀን 2011 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ የተጀመረው ሦስተኛው የመላው ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር በ20 የስፖርት ዓይነቶች እየተካሄደ ይገኛል።

በውድድሩ ከክልሎች የተውጣጡ 3ሺህ 500 ስፖርተኞች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም