የተማሪዎች ምገባ በመቋረጡ ትምህርታችንን ለመከታተል ተቸግረናል..ተማሪዎች

77

ሶቆጣ መጋቢት 18/2011 በትምህርት ቤቶች ይሰጥ የነበረው የተማሪዎች ምገባ በመቋረጡ ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል መቸገራቸውን በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሚገኙ ተማሪዎች ገለጹ፡፡

በደሃና ወረዳ የቆውዝባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ባየ አዳነ ለኢዜአ እንደገለጸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በትምህርት ቤታቸው የምገባ መርሃ ግብር ስለነበር ትምህርቱን ሳያቆራርጥ ይከታተል እንደነብር አስታውሷል፡፡

" የተማሪዎች ምገባ በዚህ ዓመት ባልታወቀ ምክንያት በማቆሙና ከቤቴ ተመግቤ ስለማልወጣ ትምህርቴን በአግባቡ መከታተል አልቻልኩም" ብሏል።

በዚህም የእለት የምግብ ፍጆታውን ለመሸፈን ሲል በቀን ሥራ መሰማራቱንና መደበኛ ትምህርቱንም መከታተል እንዳልቻለ ገልጿል፡፡

በጻግብጂ ወረዳ የምቁን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ጌታወይ ህሉፍ በበኩሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በትምህርት ቤቱ የምገባ መርሐ ግብር ተጠቃሚ በመሆኑ ትምህርቱን ያለችግር ይከታተል እንደነበር ተናግሯል፡፡

በዘንድሮ ዓመት በትምህርት ቤታቸው የምገባ አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት በሳምንት ከሦስት ቀን በላይ ወደ ትምህርት ቤት እንደማይመጣ ተናግሯል፡፡

" በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ምገባ መልሶ ቢጀምር እኔም ሆንኩ ሌሎች የትምህርት ቤት ጓደኞቼ በተሻለ ትምህርታችንን በመከታተል ውጤታማ መሆን እንችላለን" ሲልም ተማሪ ጌታወይ ተናግሯል፡፡

በትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ ግብር መኖሩ ለመማር ማስተማር ሥራው የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረው የገለጹት ደግሞ የጻግብጂ ወረዳትምህርት ጽህፈት ቤት ስርአተ ምግብ ተጠሪ አቶ ሀብቱ በላይ ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት በወረዳው በሚገኙ ሁሉም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምገባ ስርአት ይከናወን እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የምገባ መርሐ ግብሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ ከማስቻሉ ባለፈ የትምህርት ተሳትፏቸው እንዲያድግ የሚያግዝ መሆኑን አቶ ሃብቱ ተናግረዋል፡፡

"ዘንድሮ የምገባ መርሃ ግብር በመቋረጡና በሌሎች ምክንያቶች በወረዳው ለመማር ከተመዘገቡት 8ሺህ 415 ተማሪዎች ውስጥ 1ሺህ 251 ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል" ብለዋል፡፡

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያየስርአተ ምግብ ተጠሪ አቶ ፋንታው ስዩም በበኩላቸው በክልሉና በፌደራሉ መንግስት ድጋፍ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በ264 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለ141 ሺህ 700 ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት የፌደራል መንግስት በበጀት እጥረት ምክንያት ድጋፉን በማቋረጡ በክልሉ መንግስት ድጋፍ ብቻ ዝቋላ፣ አበርገሌና ሰሃላ ወረዳዎች በሚገኙ 89 ትምህርት ቤቶች ብቻ የተማሪዎች ምገባ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በእዚህም 42 ሺህ 464 ተማሪዎችን ለሦስት ወራት መመገብ የሚያስችል 4ሺህ 522 ኩንታል ምግብ ለትምህርት ቤቶች እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምገባ መርሃ ግብሩ ለመማር ማስተማሩ ስኬታማነት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የተናገሩት አቶ ፋንታው "በዘንድሮው ዓመት የተማሪዎች ምገባ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ አለመደረጉ ለተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ፋንታው ገለጻ በዘንድሮ ዓመት የተማሪዎች ምገባ በወቅቱ አለመጀመርና በአብዛኛው ትምህርት ቤቶችም መቋረጡ 7 ሺህ 998 ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ አድርጓል፡፡

በሁሉም ትምህርት ቤቶች ምገባው ካልተጀመረ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ ቁጥር ከእዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡

"ችግሩን ለማቃለል ሕብረተሰቡ በአንዳንድ አካባቢዎች እህል በማዋጣት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የምግብና ስርዓተ ምግባ ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ተዋበ አለሙ በበኩላቸው በምግባ መርሀ ግብሩ 400 ሺህ ተማሪዎች መካተት ቢገባቸውም በበጀት እጥረት ምክንያት ምግብ ማቅረብ የተቻለው ለ70 ሺህ ተማሪዎች ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወጋሶ በበኩላቸው ለትምህርት ቤቶች ምገባ መርሃ ግብር ለማካሄድ የሚያስፈልግ በጀት ዘንድሮ በመንግስት ባለመመደቡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለትምህርት ቤቶች ምገባ ሲያደርግ የነበረውን እገዛ ማድረግ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከእዚህ ቀደም የተማሪዎች ምገባ በሚካሄድባቸው ትምህርት ቤቶችን የክልል ትምህርት ቢሮዎች ምገባውን እንዲያከናውኑ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም