ባለፉት ስድስት ወራት በምመራው ክልል ሰላም እንዲሰፍን አበረታች ስራ ሰርቻለሁ-የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)

66

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2011የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ባለፉት ስድስት ወራት በምመራው ክልል ሰላም እንዲሰፍን አበረታች ስራ ሰርቻለሁ አለ።

የክልሉ ህዝቦች ለተጀመረው ለውጥ ምልዓተ ድጋፍ እንዲሰጡትም ፓርቲው ጥሪ አቀርቧል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የፓርቲውን ያለፉት ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ እንዳሉት፤ ማዕከላዊ ኮሚቴው በዛሬው ውሎው  ፓርቲው ባለፉት ስድስት ወራት ያስመዘገባቸው ስኬቶች፤ ያጋጠሙት ተግዳሮቶችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ መክሯል።

ፓርቲው የሚመራውን ህዝብ  በማስተባበር በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ማድረጉ ባለፉት ወራት በጥንካሬ የሚነሳ ስራ መሆኑን ጠቁመዋል።

"ህዝቡ ለለውጡ ስኬታማነት ያለው ምልዓተ ድጋፍ አንድ ጠንካራ ጎን ነው። ህዝቡ ሰላሙን ለማስከበር አሁን ክልሉ በተሻለ ሁኔታ ወደ ሰላም እንዲገባ ያደረገው ህዝቡ ከመንግስት፣ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ባደረገው እንቅስቃሴና የህግ የበላይነት እንዲከበር የህዝቡ ተሳትፎ እንደ አንድ ጠንካራ ጎን ነው። መዋቅሩ ህዝቡን አስተባብሮ ይህንን ተግባር በመፈጸምም እንደ ጠንካራ ጎን ነው ያየነው" ብለዋል፡፡

በፓርቲው ውስጥ ያሉት አመራሮች ለውጡ ዳር እንዲደርስ በትጋት መስራት ላይ  እኩል ቁርጠኝነት አለመያዛቸው ደግሞ በተግዳሮት የሚጠቀስ መሆኑን አውስተዋል።

ቀን ከሌት ለለውጥ የሚሰራ አመራር አንዳለ ሁሉ አሁንም ሰዓት እየቆጠረ የሚሰራ አመራር መኖሩን አልሸሸጉ ዶክተር ዓለሙ።

የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ፈቃዱ ተሰማ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለዘመናት የተከማቹና ስር የሰደዱ ችግሮች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

ኦዴፓ በእስካሁኑ ሄደቶች ያስመዘገባቸውን ድሎች አጠናክሮ ለበለጠ ስኬት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

"የፖለቲካ ችግሮቻችን ስር የሰደዱ  ናቸው። የዴሞክራሲ ባህላችን በህብረተሰብ ደረጃ አልገነባንም፤ ተቋማት አልተገነቡም፤ የህብረተሰቡ ባህል በዚህ ደረጃ አላደገም።ስለዚህ ፖለቲካችን መስከን አለበት።ከስሜት ወጥተው ወደ ስሌት መግባት አለበት የራስ መብት ሲታሰብ ስለሌላው መብት ማሰብ ተገቢ ነው የሚሆነው።የራስን መብት ለማስከበር፤ የሌላውን መጨፍለቅ አያስፈልግም። የምንከራከረው ለማሸነፍ ሳይሆን ለትከክለኛ ነገር መሆኑን ማረጋገጥ መቻል አለብን። እስካሁን ያገኘነውን ድል ይዘን ለበለጠ ድል ደግሞ እንሰራለን የሚል ቁርጠኛ አቋም አለው ኦዲፒ ።" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በፓርቲው ውስጥ በየደረጃው ያለው አመራር ከየትኛውም ጥግ የሚመጡ የልዩነት ሃሳቦችን ማስተናገድ እንዳለበት ያሳሰቡት ደግሞ ሌላኛው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቶ ኡመር ሁሴን ናቸው።

"በጣም ብዙ ነገሮች አሉ የሰውን ሰሜት የሚያነሳሱ፤ ለጥፋት የሚዳርጉ፤ አመራሩን ቢያዝ የሚያደርጉ ይሄን በጥሞና ማዳመጥ፤ ሃሳቦች ከየትኛውም አንግል ይምጡ ፤የመጣውን ሃሳብ ማስተናገድና ፤የራስን እይታ መግለጽ፤የሚያሸንፈውን የተሻለውን ተቀብሎ አብሮ መሄድ  ነው። ልዩነቶች ይኖራሉ፤ ከድርጅቱ አመራሪሮች ጋር  መሆን ያለበት ይህ ነው።" የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ውይይት ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ከውይይቱ ያገኘነው መርሃ ግብር ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም