ከአባ ሳሙኤል የኃይል ማመንጫ ግድብ ከመጋቢት 20 ጀምሮ ውሃ ስለሚለቀቅ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

91

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2011 ከአባ ሳሙኤል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከመጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ከግድቡ ውሃ የመልቀቅ ሥራ ስለሚሰራ የአካባቢው ማህበረሰብ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለኢዜኤ በላከው መግለጫ እንደገለጸው፤ ከአባ ሳሙኤል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ዓመታዊ ኃይል የማመንጨት አቅሙ 26 ነጥብ 12 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ነው።

ጣቢያው የኃይል ማመንጨት ሥራ ዳግም ከጀመረ በኋላ ከጊዜ ወደ ጊዜ የግድቡ ውሃ መጠን እየጨመረ መምጣቱን መግለጫው ጠቅሶ በግድቡ የተጠራቀመውን ውሃ በመልቀቅ በሚወርደው የወንዝ ውሃ ብቻ ኃይል ለማመንጨት እንደሚሰራ አስታውቋል።

በመሆኑን ከመጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በግድቡ የወለል ማስተፍንሻ ከፍተኛ ውሃ እንደሚለቀቅ ገልጿል።

በዚህም በሚለቀቀው ውሃ ከግድቡ በታችኛው ተፋሰስ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ወንዙ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስቀድማችሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

የአባ ሳሙኤል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግድብ በ1933 የተገነባ ጣቢያ ሲሆን ከ1967 ጀምሮ አገልግሎት መስጠት አቋርጦ ቆይቶ ከህዳር 2009 ዓ.ም ጀምሮ የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

''ግድቡ ከ40 ዓመት በላይ ስራ በማቆሙ የአካባቢው ነዋሪዎች በግድቡ ዳርቻዎች የእርሻ ስራ ያከናውኑበት ነበር'' ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም