የአቶ ኢሳያስ ዳኘው ጠበቆች ያቀረቡት ሁለተኛ የክስ መቃወሚያ የህግ መሠረት እንደሌለው ዐቃቤ ህግ አስታወቀ

117

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2011 የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የአቶ ኢሳያስ ዳኘው ጠበቆች ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ የህግ መሠረት የለውም ሲል ተከራከረ።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ. ም በዋለው ችሎት ዐቃቤ ህግ በአቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ የመሠረተውን ክስ አሻሽሎ እንዲቀርብ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።

ዐቃቤ ህግ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተከትሎ በስድስት ጭብጦች በአቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ ክሱን አሸሽሎ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ ባስቻለው ችሎት የአቶ ኢሳያስ ዳኘው ጠበቆች ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ክሱ እንዲሻሻል ትዕዛዝ ከሰጠበት ጭብጥ ውጭ መሆኑን ዐቃቤ ህግ አመልክቷል።

ከተከሳሽ የወንጀል አፈጻጸምና ድርሻ አንጻር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር የቀረበ ጥያቄ የለም የሚለውን ወንጀሉ ከተፈጸመበት ቀን አንጻር 'በምን እናስታርቀው' የሚለውን በተመለከተና የ'ቬንደር ፋይናንሲንግ አግሪመንት' ከግዥ መመሪያው አንጻር የቀረበው መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ክሱ እንዲሻሻል ካዘዘበት ጭብጥ ውጭ የሆነ አዲስ ፍሬ ነገር ነው።

የተከሳሽ ጠበቆች በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ያላነሱት አዲስ ፍሬ ነገር በመሆኑ የቀረበው የክስ መቃወሚያ ተገቢነት እንደሌለው በመግለጽ ተከሳሽ ያላነሳቸው ፍሬ ነገሮች ካሉ በዋና ክርክርና በማስረጃ የሚረጋገጥ ጉዳይ እንደሆነ በመግለጽ ዐቃቤ ህግ ተከራክሯል።

እንዲሁም ተከሳሽ ለቀረበባቸው ክስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በሚያቀርቡበት ወቅት በክስ መቃወሚያቸው ላይ የሚያነሷቸውን ፍሬ ነገሮች በማካተት ወዲያውኑ ማቅረብ እንዳለባቸው በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ሥነ ስርዓት ቁጥር 130 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ መደንገጉን አመልክቷል።

ተከሳሽ ለቀረበባቸው ክስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ባቀረቡበት ወቅት ያላነሷቸውን አዲስ ጉዳይ ካላቸው በዋና ክርክር እና በማስረጃ የሚረጋገጥ እንጂ የክስ መቃወሚያ የሚቀርብ ጉዳይ ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ የቀረበውን የክስ መቃወሚያ ውድቅ እንዲያደርግ ዐቃቤ ህግ ጠይቋል።

በተጨማሪም ክሱ ተሻሽሎ የቀረበው ፍርድ ቤቱ ብይን በሰጠባቸው ጭብጦች መሠረት በመሆኑ የተከሳሽ ጠበቆች በወቅቱ ያቀረቡት ተቃውሞ ባለመኖሩ በተሻሻለው ክስ መሠረት ክርክሩ እንዲቀጥል ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቋል።

የተከሳሽ ጠበቆች በመጀመሪያ መቃወሚያ ሊቀርቡ የሚገባቸውን ነጥቦች ወዲያውኑ ለፍርድ ቤት ሳያቀርቡ ከቀረ የክስ መቃወሚያው እንደተተወ ይቆጠራል።

የዐቃቤ ህግን የቃል ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም