የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተገቢውን የሥራ ዕድል እየፈጠረልን አይደለም... የአካባቢው አርሶ አደሮችና ወጣቶች

49

አዳማ መጋቢት 17/2011 የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተገቢውን የሥራ ዕድል እየፈጠረልን አይደለም ሲሉ የመሬት ይዞታቸውን ለፓርኩ ግንባታ የለቀቁ የአካባቢው አርሶ አደሮችና ወጣቶች ቅሬታቸውን ገለጹ።

በአዳማ ከተማ ቦኩ ሸነን ቀበሌ ገበሬ ማህበር የሚኖረው ወጣት ሻንቆ አራርሳ ለኢዜአ እንዳለው ለልማቱ ከይዞታቸው ሲነሱ ቅድሚያ የአካባቢው ነዋሪዎች በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሥራ ዕድል እንደሚመቻችላቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር።

"የተሻለ የካሳ ክፍያ ያገኘን ጥቂት አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው አሸዋና ጠጠር ለፓርኩ እያቀረብን ብንሆንም ክፍያ ሳይፈፀምልን እስከ አምስትና ስድስት ወራት እንቆያለን ሲል" ተናግሯል።

በዚህም አርሶ አደሩ ልጆቹን ለመመገብና ለማስተማር እየተቸገረ መሆኑን የተናገረው ወጣት ሻንቆ የአካባቢው ወጣቶች በጫኝና አውራጅ ሥራ ተደራጅተው ለመስራት እንዳልቻሉም ገልጿል።

በፓርኩ ሥራ የጀመረው የቻይና ኩባንያ በጫኝና አውራጅ የተደራጁትን የአካባቢውን ወጣቶች ሥራ በመከልከል ሥራውን በቻይናዎች እያሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአርሶ አደር ልጆች በጉልበታቸው ሠርተው የሚበሉበት አማራጮች እንዲመቻችላቸውም ጠይቋል።

"አርሰን ስንጠቀምበት የነበረውን የመሬት ይዞታ ለልማቱ የለቀቅነው ልጆቻችን ከልማቱ ይጠቀማሉ በሚል እምነት ነው" ያሉት ደግሞ አርሶ አደር በቴ ቀዲዳ ናቸው።

"ቻይናዎች ሳይቀሩ የጫኝና አውራጅ ሥራን ከልጆቻችን እየተሻሙ ነው" ያሉት አርሶ አደሩ መንግስት ባለሀብት ለማምጣት ሲል ብቻ የህብረተሰቡን ጥቅም መጉዳት እንደሌለበት አመልክተዋል።

የአካባቢው ወጣቶች በጥበቃ ሠራተኝነት እንዳይቀጠሩም የጥበቃ ቀጣሪ አጄንሲዎች ከኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ጋር በመሆን ሠራተኞችን ቀጥረው ስለሚልኩ ልጆቻቸው ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

"በትምህርት የገፉ ልጆችም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ለመቀጠር ያላቸው እድል የጠበበ ነው" ያሉት አርሶ አደር በቴ የሚመለከተው የመንግስት አካል ለጥያቄያቸው ተገቢ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ብሩ ዳዲ በበኩሉ " በአሁኑ ወቅት ተደራጅተን እየሰራን ያለነው የተወሰን ሰዎች ነን፤  አንዳንድ አርሶ አደሮች በገንዘብ አያያዝ ችግር ምክንያት የተሰጣቸውን የካሳ ገንዘብ ጨርሰዋል" ብሏል።

"ብዙ የአካባቢው ወጣቶችና አርሶአደሮች ጉልበት በሚጠይቅ የሥራ መስክ እንኳን መሳተፍ አልቻሉም፤ ይህን ጥያቄያችንን ለከተማ መስተዳደሩና ለኢንዱስትሪ  ኮርፖሬሽን ብናቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘንም " ብሏል።

የአዳማ ከተማ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብደላ ገሞ በበኩላቸው ለልማት ተነሺዎች በፓርኩ የሥራ እድል ከመፍጠር አንፃር አሁንም እያጋጠሙ ያሉ ቁልፍ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

መንግስት ባለሀብቶችን ከውጭ ሲያመጣ ስለ ሀገሪቷ ህግ በትክክል እንዲገነዘቡ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረው አርሶ አደሩ ብቻኛ ሀብቱን ለቆ ሜዳ ላይ ሊወድቅ እንደማይገባ አመልክተዋል።

" ኤጄንሲዎች ከኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ጋር በመሆን ለእኛ ሳያሳውቁ ጥበቃዎችን ከሌላ አካባቢ ቀጥረው እያስገቡ በመሆኑ በአካባቢው አርሶ አደሮች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል" ብለዋል።

በእዚህም በጫኝና አውራጅ የተደራጁ ወጣቶች የሥራ ዕድል ሳያገኙ  ሥራው በቻይናዎች የሚሰራበት ሁኔታ እንዳለ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት ከክልሉ መንግስትና ከኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመነጋገር እየሰሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በፓርኩ ጉብኝት ያደረጉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቡድን መሪ አቶ ጌታቸው ለማ በበኩላቸው ማንኛውም ኢንቨስትመንት የአካባቢውን የልማት ተነሺዎች ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በፓርኩ የተሰማሩ የውጭ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች የሀገሪቷን ህግና ደንብ አክብረው መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ በመስክ ምልከታው ወቅት የታዘቡትን ለክልሉ መንግስትና ለፌዴራል መንግስት በማቅረብ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥበት ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም