የኢትዮጵያና ቱርክ የንግድ ልውውጥ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል እየሰራን ነው - አምባሳደር ፋቲህ ኡልሶይ

111
አዲስ አበባ ግንቦት 24/9/2010 በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ኡልሶይ ተናገሩ። ሁለቱ አገሮች የጀመሩት የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት ለወዳጅነታቸው መጎልበት ትልቅ ሚና እንዳለው አምባሳደሩ አክለዋል። ኢትዮጵያና ቱርክ ሺህ ዓመታትን ወደ ኋላ የሚሻገር የንግድ ልውውጥ እንዳላቸው በርካታ የታሪክ ድርሳናት የሚያወሱ ሲሆን፤ የንግድ ልውውጡም በገንዘብ ሲመዘን የቆይታውን ያህል ሚዛን የሚደፋ አይደለም። በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 400 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን እ.ኤ.አ በ2000 አሃዙ 27 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር። አምባሳደር ፋቲህ ኡልሶይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ እንዲጎለብትና አሁን ያለው የንግድ ልውውጥ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል መንግስታቱ መጠነ ሰፊ ውይይቶችን እያደረጉ ነው። በአሁኑ ወቅት 150 የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማውጣት እየሰሩ በመሆናቸው 30 ሺህ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል መፍጠራቸውን አውስተዋል። ቱርክ በኢትዮጵያ ያላት አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ምጣኔ 2ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላር መደረሱንም አክለዋል። በርካታ ቱርካውያን የቢዝነስ ልኡኮች በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ልኡኮችም የቢዝነስ ዘርፍ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መስሪያ ቤቶች ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር መቻላቸውን ገልጸዋል። ከቢዝነስ ልኡኮች መካከል ጥቂት የማይባሉት አማራጭ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነት አምባሳደሩ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ቱርክና ኢትዮጵያ የጀመሩት የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት ለሁለቱ አገሮች ትስስር መጎልበት ትልቅ ሚና እንዳለው አምባሳደር ፋቲህ ጠቁመዋል። በቅርቡ የቱርክ የፓርላማ አባላት በአገሪቱ በሰኔ ወር ለሚደረገው ምርጫ የሚያደርጉት የምረጡኝ ዘመቻ ሳይገድባቸው ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ቱርክ ለኢትዮጵያ ያላትን አጋርነት ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል። አምባሳደር ፋቲህ ኡልሶይ በአገራቸው ከሚካሄደው ምርጫ በኋላ የቱርክ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያሳተፈ ልዑክ ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ቱርክ በአፍሪካ ያላት ኢንቨስትመንት 6ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፤ አገሪቱ ከአፍሪካ አገሮች ጋር የምታደርገው የንግድ ልውውጥም 17 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም