የላሟን መልክ ቀይሮ ገበያ ያወጣው ግለሰብ ተቀጣ

112

ጅማ መጋቢት 17/2011 ጉድ ሳይሰማ መስከርም አይጠባም እንዲሉ በመሰንበቻው  ከወደ ጅማ ዞን የተሰማው አስገራሚ ጉዳይ እንዲህ ይገለጻል፡፡ 

ጉዳዩ በጅማ ዞን  ሸቤ ሶምቦ ወረዳ በተለምዶ ሃሏ ሰቦቃ ልዩ ስሙ ገሬ ገነታ በሚባለው አካባቢ የተፈጸመ ነው፡፡

ይህም የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀኑ አስር ሰዓት አካባቢ  ባለቤትነቷ የአንድ ግለሰብ የሆነች  ቀይ ቀለም ያላት ላም ትጠፋለች፡፡

በማግስቱ ይቺ ላም ሌላ ግለሰብ   ቀለም ቀብቶ ቀይ የነበረችውን ወደ ዳለቻ በመቀየር ገበያ ወስዶ ለሽያጭ ያቀርባል፡፡

የሸቤ ሶምቦ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ  ረዳት ሳጂን አማኑኤል ዋቅጅራ  እንዳስረዱት በሰዎች  ጥቆማ ላማቸው በአካባቢው ገበያ ለሽያጭ መቅረቧን መረጃ  የደረሳቸው የላሟ ባለቤት  በቦታው ሄደው እንዲያዩ ቢደረግም የእሳቸው ስለመሆኑ ለይተው ሊውቁ አልቻሉም፡፡

ጉዳዩን ለማጣራት በተደረገው ጥረት ተጠርጣሪው ግለሰብ ድርጊቱን እንደፈጸመ ተደርሶበት በህብረተሰቡና በፖሊስ ትብብር ገበያ እንዳለ በዕለቱ ሊያዝ ችሏል፡፡

የላሟ ባለቤትም የኋላ ኋላ የእሳቸው መሆኗን ማረጋገጣቸውን ረዳት ሳጂን አማኑኤል አስረድተዋል፡፡

ፖሊስ ጉዳዩን አጠርቶ የካቲት14 ቀን 2011 ዓ.ም. በግለሰቡ ላይ ፍርድ ቤት ክስ መስርቷል፡፡

ክስ የቀረበለት የወረዳው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ሲመረምር ከቆየ በኋላ መጋቢት 5 ቀን 2011ዓ.ም. በዋለው ችሎት በስርቆት ወንጀል የተጠረጠረው  ተማም አባጎጃም ጥፋተኛነቱን በማረጋገጥ በሁለት ዓመት ከአራት ወር እስራት እንደቀጣ ተወስኖበታል፡፡

ግለሰቡ ክሱን እንዲከላከል እድል ቢሰጠውም ባለመቻሉ ቅጣቱ ጸድቆበታል፡፡

የተሰረቀችውን ላም ባለቤቷ እንዲረከቡ ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም