በአዲስ አበባ ጤና ጣቢያዎች የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ኤክስቴንሽን ትምህርት ሊጀምሩ ነው

82

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2011 በአዲስ አበባ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በከተማዋ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ኤክስቴንሽን ትምህርት ሊጀመር ነው።

በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ 98 ጤና ጣቢያዎች የመንገድ ትራፊክ አደጋ መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን የተመለከተ መረጃና ትምህርት ለመዲናዋ ነዋሪዎች ይሰጣል። 

ይህንኑ መርሃ ግብር በጋራ መተግባር ይቻላቸው ዘንድ የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና የጤና ቢሮ ዛሬ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በኢትዮጵያ በሚከሰቱ የመንገድ ትራፊክ አደጋዎች ሳቢያ በየዓመቱ የ5 ሺህ ሰዎች ህይወት እንደሚጠፋ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ህይወታቸው ከሚያልፈው እነዚህ ኢትዮጵያዊያን መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉ ወጣቶችና ጎልማሳ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። 

በአገሪቱ በአሳሳቢ ደረጃ አየተስፋፋ የመጣው የትራፊክ አደጋ ከሰው ህይወት ባሻገር በሚሊዮኖች ለሚገመት ንብረት ውድመትም ምክንያት እየሆነ መምጣቱም ይነገራል።

የመዲናዋ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና የጤና ቢሮው ዛሬ የፈረሙት ስምምነት ይህንን ሰብአዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳት መቀነስ ይቻል ዘንድ የህብረተሰብ ግንዛቤ ላይ ያተኮረ የትራፊክ አደጋ መከላከል መርሃ ግብርን በጋራ መተግበር ነው።

በስምምነቱ መሰረት በአዲስ አበባ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ኤክስቴንሽን ቡድን ይቋቋማል፤ ቡድኑም የመንገድ ትራፊክ አደጋ መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን የተመለከተ መረጃና ትምህርት  ለመዲናዋ ነዋሪዎች ይሰጣል። 

የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ግርማ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ስምምነቱ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ደርሶ ህይወት የማዳን ስራ ከመጠመድ ይልቅ አደጋን ቀድሞ ለመከላከል ያግዛል።

በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ 98 ጤና ጣቢያዎች በየቀኑ በሚሰጠው የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ውስጥ የመንገድና ትራፊክ ደህንነት ትምህርት እንዲሰጥ የሚደረግ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም አደጋን ቀድሞ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ። 

በአጠቃላይ በመንገድ ደህንነት ውስጥ ያሉ የዘርፉ ተዋናዮችም በጋራ መስራት የሚችሉበትን ቅንጅታዊ ስርዓት ለመዘርጋትም ስምምነቱ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።

የመንገድ ትራፊክ አደጋ የሚያስከትለው ጉዳት በአሁኑ ሰአት እንደ ተላላፊ ያልሆነ በሽታ ተቆጥሮ ቀድሞ መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጋራ የመስራት እንቅስቃሴ እየተከናወነ መሆኑንና ስምምነቱም የዚሁ አካል እንደሆነም አክለዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ሳሙኤል ዘመንፈስቅዱስ በበኩላቸው ስምምነቱ ከድህረ አደጋ ምላሽ ይልቅ ቅድመ አደጋን መከላከል ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በአደጋዎች ምክንያት የሚደርሰውን ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት መቀነስ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ለግንዛቤ ማስጨበጫው ይረዳ ዘንድ በየክፍለ ከተማው በሚገኙ ጤና ጽህፈት ቤቶች አማካኝነት ባለሙያዎችና አስተባባሪዎች እንዲመለመሉ መደረጉንና ለተመለመሉት ባለሙያዎችና አስተባባሪዎች ስልጠና እንደተሰጠ ተናግረዋል።

ስምምነት የፈረሙት ተቋማትም በጤና ጣቢያዎቹ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርሱትን የሞትና ከባድ ጉዳት መረጃዎችን አጠናክረው እንደሚይዙም ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በአዲስ አበባ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ ባለው የመንገዶች ከትራፊክ ነጻ ቀን ላይም በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኙም በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም