የዴንማርክ ንግስት ሜሪ ኤልሳቤት ኢትዮጵያ የሴቶችና የህፃናትን ጤና አጠባበቅ ስርዓትን አደነቁ

72

አዲስ አበባ  መጋቢት 17/2011 በኢትዮጵያ እየተሻሻለ የመጣውን የሴቶችና የህፃናት ጤና አጠባበቅ የዴንማርክ ንግስት ሜሪ ኤልሳቤት አደነቁ።

ንግስቲቷ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ሲሆኑ በዛሬው እለትም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ  ቅርንጫፍ የሆነውን የምቹ ክሊኒክ የስነ ተዋልዶና የመካንነት የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ተመልክተዋል።

በጉብኝታቸው ተገልጋዮችን ጨምሮ፣ ከነርሶችና ከዶክተሮች ጋር የተነጋገሩ ሲሆን ኢትዮጵያ እንደ አገር ለሴቶችና ለህፃናት ጤና ትኩረት መስጠቷን መገንዘብ መቻላቸውን ተናግረዋል።

ንግስቲቷ በሆስፒታሉ የማህፀንና የፅንስ ስፔሻሊስት እንዲሁም የምቹ ክሊኒክ እንዲመሰረት ከፍተኛ ጥረት ካደረጉት ፕሮፌሰር ሰናይት ፍስሃ ጋር የተወያዩ ሲሆን ኢትዮጵያ የሴቶችና የህፃናትን ጤና ከመጠበቅና የፆታ እኩልነትን ከማስከበር ረገድ ያመጣችውን ለውጥ ማድነቃቸውን ፕሮፌሰሯ ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ የስነ ተዋልዶ ህክምና መስጫ የሚገኙ ዘመናዊ የህክምና ቁሳቁሶችንና በቅርቡ አገልግሎት የሚጀምረውን የመካንነት ህክምና መስጫ ማዕከል ጎብኝተዋል።

ፕሮፌሰር ሰናይት እንዳሉት፤ በተለይም በቤተስብ ምጣኔ፣ የእናቶችና ህፃናት ሞትን በመቀነስ ረገድ ያለው እድገት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እንዳመጣችው ለውጥ ሁሉ የሴቶች እኩልነትና ተሳታፊነትን ከማመጣጠን አኳያም ትልቅ እድገት ማስመዝገቧን  መመልከታቸውን ፕሮፌሰሯ ተናግረዋል።

''ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የፆታ እኩልነትን፣ ፆታዊ ጥቃትንና ሴቶችን ለማብቃት ያለሙ በርካታ የህግ ማዕቀፍ በማውጣት ረገድ የተዋጣላት ብትሆንም አተገባበሩ ላይ ቀሪ ስራ ስለመኖሩ አስተያየት ሰጥተዋል'' ብለዋል።

ዴንማርክ በጤና፣ ሴቶችን በማብቃት፣ በፆታዊ እኩልነትና በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች ለኢትዮጵያ ድጋፍ የምታደርግ ሲሆን ከ2018 እስከ 2022 ድረስ የሚፈፀም በኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ድጋፍ  አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም