በመስዋዕትነትና በጋራ ርብርብ የተገኘው ለውጥ በማንኛውም ሙከራ ወደ ኋላ አይቀለበስም -ኦዴፓ

103

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2011 በመስዋዕትነትና በጋራ ርብርብ የተገኘው  ለውጥ በማንኛውም ሙከራ ወደ ኋላ የማይቀለበስ መሆኑን  በድጋሚ ያረጋግጣል ሲል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ገለጸ።

የኦሮሞ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) 29ኛውን የምስረታ በዓል እና የአንደኛው ዓመት የለውጥ ጉዞን አስመልክቶ “መደማማጥ ለቀጣይ የስኬት ጉዞ ” በሚል መሪ ሐሳብ ትናንት ባወጣው መግለጫ ትግሉ የሚጠይቀውን ማንኛውንም መስዋዕትነት በመክፈል የተጀመረውን ትግል ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ኦዴፓ ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዳለው አረጋግጧል፡፡

ነገ ለሁላችን የምትሆን አገር የመጠበቅ ጅማሮ እንዲሁም በየፈርጁ እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች መሬት ይዘው እንዲቀጥሉና አንዲሻገሩ በመስራት ላይ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ ያቀረበው መግለጫው፤ መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከወንድም የኦሮሞ ህዝብ ጋር በመሆን እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።

ህዝቡ በተለይም ወጣቱ የሚያደርገውን ማንኛውንም ትግል በተደራጀ ፣ ከስሜታዊነት በነፃ ፣ በተረጋጋ፣ ብስለት በተሞላበትና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መሆን  እንዳለበት አመላክቷል መግለጫው።

በመሆኑም የክልሉና መላው የአገራችን ህዝቦች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ተወካዮችም የተጀመረውን ትግል ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ሂደት ከፓርቲው ከኦዴፓ ጎን እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ODP) 29ኛው የምስረታ በዓል እና የአንደኛው ዓመት የለውጥ ጉዞን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

“መደማማጥ ለቀጣይ የስኬት ጉዞ ” !

የኦሮሞ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ODP) ታሪክ እንደሚያስታውሰው በማናቸውም የትግል ምዕራፎች ውስጥ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሲደርስ በነበረው ጭቆናና አድሎ ሕዝቡ የሚያነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ብዙ ውጣ ውረዶች ዉስጥ አልፎ ዛሬ ላይ የደረሰ ፓርቲ ነዉ፡፡

የኦሮሞ ሕዝብና የኦሮሞ ታጋዮች የታገሉላቸውና ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉበት የፖለቲካ፣የኢኮኖሚና የማህበራዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት መብቶች ፍሬያማ እንዲሆኑ የኦሮሞ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ODP) ባካሄደው መራራ ትግል በታሪክ የሚወሱ በርካታ ድሎችን ለማስመዝገብ ችሏል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ሕዝብ በአገር ግንባታ ውስጥ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከመደበቅ አልፎም መሰረታዊ ጥያቄዎቹ ሰሚ በማጣታቸው ከአርሶ አደሩ ትግል ጀምሮ ትውልዶች መስዋዕትነት የከፈሉባቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እንዲሁም የሕዝቡን ትግል ፈር ማስያዝና ማሻገርን ማዕከል አድርጎ በችግር ውስጥ የተመሰረተ፣በችግር የተፈተነና ሕዝቡን ከሰቆቃ ያዳነ ፓርቲ ለመሆኑ ትዉልድ የሚያስታዉሰዉ ነዉ፡፡

የኦሮሞ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ODP) በአገሪቱ ውስጥ ሕዝቡ የታገለላቸው የመብት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙና የኦሮሞ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሱን መንግስት የመመስረትና ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት እንዲጎናጸፍ ያስቻለ ነው፡፡

ትዉልድ በራሱ ቋንቋ እንዲማር፣ብሎም የክልሉ መንግስት የስራ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ ሆኖ እንዲያገለግል በፓርቲያችን ትግል በተቀየሰው መንገድ በቋንቋችን ህገ መንግስት ጽፈን፣ ጨፌ ተቀምጠን፣ ምዕተ ዓመታትን የሚሻገር አኩሪ ተግባር አከናዉነናል፡፡

በትግሉ ሂደትም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዉስጥ ከህብረተሰቡ ፍላጎት መጨመር ጋር ተያይዞ የተለያዩ ጥቄዎች ከህብረተሰቡ መቅረብ ጀምረዋል፡፡

ዛሬ በአለማችን ዕድገት በማሳየት ዜጎቻቸዉን በተድላ ማኖር የቻሉ ሀገሮች የኋላ ታሪካቸዉ ሲታይ ከህዝቦቻቸዉ የሚቀርበዉን ቅሬታና እምቢታን፣ ወጣቶች የሚያደርጉትን አመጽ በዲሞክራሲያዊ መንገድ በመፍታትና ቀጣይነት ያለዉ ልማት ማረጋገጥ በመቻላቸዉ ነዉ፡፡

ፓርቲያችንም ከዕድገት ጋር ተያይዘዉ የሚነሱ ችግሮችን እና እንዲታረሙ የተጠቆሙ ጉድለቶች በመፍታት ባህሉ ይታወቃል፡፡

የፓርቲያችን ዲሞክራሲያዊነትና ህዝባዊነት በማንኛዉም መንገድ ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን በማዳመጥ ከልብ ይቅርታ በመጠየቅና የማስተካከያ እርምጃ መዉሰድ ትክክለኛ መሆኑን በማመን ወደ ተግባር ለመቀየር እያጎለበተ በመምጣቱ ጥልቅ ተሃድሶ ዉስጥ በመግባት ጉዞዉን ሊያድስ ችሏል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የፖለቲካ ጥያቄዎችና ለፓርቲዉም መመስረት ምክንያት የሆኑ አበይት ጥያቄዎችን በቅደም ተከተል በማስቀመጥ፣ አቅጣጫ በማስያዝ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት በጠብመንጃ አፈሙዝና በጥላቻ ማሸነፍ እንደማይቻል በመገንዘብ በመደመር ፍልስፍና በሀሳብ መሸናነፍ እንዲቻል ውስጣዊ ትግል በማካሄድ ታሪክ የሰሩ ታጋዮችን ያፈራ ፓርቲ ነዉ፡፡

ፓርቲያችን በዜጎች እስር ቤትነት የምትታማዋን ሀገር ከመፍረስ በማዳን የሀገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ስነ ልቦናን ከእስር መፍታት ተችሏል፡፡

ኦሮሞነት በመወያያትና በአንድነት መሆኑን በማመን በኦሮሞ ስም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ የታሰረ ከእስር እንዲፈታ፣ የተሰደደ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ያስቻለ ፓርቲ ነዉ፡፡

በዚህ ሀገር በእስር ቤት ፍዳ ሲያዩ የነበሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲፈቱ፣ የምሁራን ተሳትፎ እንዲያድግ፣ መሰረት የጣለ ፓርቲ ለመሆኑ ከብሄር ብሄረሰቦች ባሻገር ከዓለም አቀፍ ዕውቅና የተቸረው ፓርቲ ነዉ፡፡

ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በፖለቲካ ዕኩል ተሳትፎና በጠንካራ ዲሲፕሊን በመተግበር የሰፊዉን የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት ለማሟላት በሌቦች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችና የኦሮሞ የኢኮኖሚ አብዮት ለህዝቡ ተስፋን የሰነቀ ነዉ፡፡

መከባበርና ወንድማዊ አብሮ መኖር የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋር ያለው ጥንታዊ የገዳ ስርዓት እሴት እና ሀገርን በመገንባት ረገድ ከሀገር ውስጥ እርቅ በዘለለ ለጎረቤት ሀገሮች ባደረገው ፓርቲያችን ዓለም ያደነቀዉ መሪ ያፈራ ነዉ፡፡

የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግር ከመፍታት ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከስረ መሠረቱ ለመፍታት የመንግስታዊ መዋቅር ሪፎርም፣ ፍትሃዊ አገልግሎት ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች የህዝባችንን ፍላጎት ላይ መሠረት ከማድረግ ባሻገር የሀገራችንና የአካባቢያችንን የወደፊት ህልዉና ላይ የተመሠረተ ነዉ፡፡

ኢኮኖሚያችንን ከሚያቀጭጩ ድርጊቶች ለምሳሌ እንደ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ኮንትሮባንድ፣ የንግድ ገበያን የሚያደናቅፉ ውስብስብ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን በመበጣጠስ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራር በመዘርጋት የንግድ ስርዓቱን ለማቀላጠፍ የተቀመጠዉ አቅጣጫ ውጤት በማስገኘት ላይ ይገኛል፡፡

የገቢ ምንጭን በማሳደግ፣ የገንዘብ አስተዳደርን በማሻሻል ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር በኢኮኖሚ አብዮት ውስጥ በልዩ ሁኔታ የሚታይ የኦዴፓ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

እንደ ክልላችንም ሆነ እንደ ሀገራችን ሰላምና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የፖለቲካ ነጋዴዎች በተለያየ መንገድ ዛሬ የታየው ተስፋ እነሱን ስለሚጎዳ ለማደናቀፍ በሚፈልጉ ሀይሎች እንዳይደናቀፍ ፓርቲያችንና በፓርቲያችን የሚመራዉ መንግስታችን አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ላይ ይገኛል፡፡

የኦሮሞ ህዝብና የሀገራችን ህዝቦች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በቅደም ተከተል በጥናት ላይ በመመርኮዝ በሰከነ መንገድ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ኦዴፓ የጀመረቸዉን ስራዎች በመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በውድ መስዋዕትነትና በጋራ ርብርብ በተገኘው የሽግግር ለውጥ በማንኛውም ሙከራ ወደ ኋላ የማይቀለበስ መሆኑን ኦዴፓ በድጋሚ ያረጋግጣል፡፡

ትግሉ የሚጠይቀውን ማንኛውንም መስዋዕትነት በመክፈል የተጀመረውን ትግል ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የአገራችንን ሕዝቦች መብትና ጥቅም ለማስከበር ኦዴፓ በከፍተኛ ቁርጠኝነት የጀመረውን ትግል ከምን ጊዜውም በበለጠ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ኦዴፓ ህዝቡን የኋላ ደጀን በማድረግ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በማንኛውም አውሎ ንፋስ አይገፋም፤ ማንኛውም የጥፋት ሙከራ አያደናቅፈውም፡፡ ኦዴፓ የአገሪቷን ህዝቦች የነገ ብሩህ ተስፋ ለማስፈንጠቅ ይሰራል፡፡

የተከበርከው የኦሮሞ ሕዝብ!

ከተቀሩት የአገሪቷ ሕዝቦች ጋር በመሆን ረጅም ጊዜ የፈጀ የመብት ትግል ስታካሂድ ቆይተሃል፡፡

ባካሄድከው መራራ ትግልና በከፈልከው ውድ መስዋዕትነትም ለነገይቱ ሀገራችን ተስፋ የፈነጠቀና ዓለምም የመሰከረለት አንፀባራቂ ድል በአጭር ጊዜ ውስጥ አስመዝግበሃል፡፡

አንተ በከፈልከው መስዋዕትነት ተስፋ ሰጪ ድሎች ቢመጡም በተፈጥሮው ለውጥ ወቅት ሊያጋጥሙ በሚችሉ ችግሮችም ይሁን የታዩትን የነገ ተስፋ ጅማሮዎችን ሊያደናቅፉ የሚችሉ አሰራሮችና አመለካከቶች ሁሉ ገና ፈር ያልያዙ በመሆናቸው ይህንን ብሩህ ተስፋ ሊያጨልሙ የሚችሉ ችግሮች እያጋጠሙ ይገኛሉ፡፡

ስለዚህ እነዚህ ለዕድገትህ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ለማስተካከል ለዓለም ባበረከትከው የዲሞክራሲ ባህልና ትውፊት ላይ በመመርኮዝ የጀመርከውን ትግል አጠናክረህ መቀጠልህን ዓለም በበጎ መልኩ እያስተዋለው ይገኛል፡፡

ታሪክ በሚያስታውሰው በማንኛውም የትግል ምዕራፍ ውስጥ ለገዢ መደቦች ጭቆናና አድልዎ አልንበረከክም በማለት ከተቀሩት ወንድማማች የአገራችን ሕዝቦች ጋር በመሆን መስዋዕትነት እየከፈልክ ድል እየተጎናፀፍክ እንደቆየህ ሁሉ አሁንም እያጋጠሙህ ያሉ ችግሮችን ከትውልዶች በወረስከው አኩሪ የገዳ ባህልህን በመጠቀም የተቀሩትን የአገሪቱ ሕዝቦችን በፍቅር ያቀፈ ወቅቱ የሚጠይቀውን መራራ ትግል እንድትቀጥልና ነገ ለሁላችን የምትሆን አገር የመጠበቅ ጅማሮ እንዲሁም በየፈርጁ እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች መሬት ይዘው እንዲቀጥሉና አንዲሻገሩ እያደረክ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክረህ እንድትቀጥል ኦዴፓ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ለተከበራችሁ የኦሮሞ ቄሮና ቀሬዎች !

በክልላችንም ሆነ በአገር ደረጃ መመዝገብ የጀመሩ ለውጦች ግንባራችሁን ለጦር በመስጠት በከፈላችሁት ውድ መስዋዕትነት የመጡ ናቸው፡፡

በመሆኑም ኦዴፓ በክልላችንም ሆነ በአገር ደረጃ እስካሁን የታዩ ለውጦች በቄሮዎችና ቀሬዎች መራራ ትግልና ሰፊ ተሳትፎ የመጣ ነው ብሎ ያምናል፡፡

ይህ በውድ መስዋዕትነት የመጣውን ለውጥ መቀልበስ የሚፈልጉ ኃይሎች ነካክተውን ስሜት ውስጥ እንድንገባ ይፈልጋሉ፡፡

የህግ የበላይነት ተጥሶ ለውጡ እንዲደናቀፍ እልህ ውስጥ ሊያስገቡን ይፈልጋሉ፡፡

ስለዚህ ቄሮዎችና ቀሬዎች የሚያደርጉት ማንኛውም ትግል በተደራጀ ፣ ከስሜታዊነት በነፃ ፣ በተረጋጋ፣ ብስለት በተሞላበትና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መሆን አለበት፡፡

እንዲሁም የተገኙ ለውጦችን እየተንከባከባችሁ ለነገው ተስፋና የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል ዛሬም እንደትላንቱ በግንባር ቀደምትነት የምታበረክቱትን አስታዋጽኦ እንድትቀጥሉበት ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የሃገራችን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች!

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወንድም ከሆነዉ የኦሮሞ ህዝብ ጋር በየዘመናቱ ያጋጠሙትን ችግሮች ተደጋግፋችሁ በመታገል አልፋችሁታል፡፡

በጋራም መስዋእትነት ከፍላችኋል፡፡ ደስታም ተጋርታችኋል፡፡

ዛሬ አንዳንድ የፖለቲካ ነጋዴዎች አነዚህን ወንድማማች ሕዝቦች በማጋጨት እነሱ በእሳት ሲቃጠሉ ከዳር ሆነው ለመሞቅ ይሻሉ፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ፣ መንግሥትና ኦዴፓ ዛሬም እንደትላንቱ የሕዝቦች በወንድማማችነት አብሮ መኖር፣ መልካም ባህሎችን መጋራት፣ የጋራ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ልምድ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ፅኑ አቋም አላቸው፤ለዚህም በቆራጥነት ይሰራሉ፡፡

ስለዚህ ኦሮሚያ የብሔሮችና ብሔረሰቦች ማዕከል ናት፡፡ የኦሮሞ ሕዝብም በአቃፊነቱ ይታወቃል፤ ብሔሮችና ብሔረሰቦችን ለማጋጨት የሚደረገው ሙከራና የተንኮል ፖለቲካ ንግድ ቦታ እንዳያገኝ በማጋለጥ እንደ ትላንቱ ወንድማችሁ ከሆነው ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በመሆን የጀመራችሁትን የአገር ግንባታ ርብርብ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ኦዴፓ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

አባቶቻችን በመስዋዕትነት ያወረሱንን ሀገር አንድነቷን ጠብቀን ለማስቀጠል የታሪክ ተጠያቅነት አለብን ፡፡

ይህንን ተጠያቂነት ለመወጣት የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነትን በማጠናከር የጋራ እሴቶቻችንን በማጎለበት ፓርቲያችን የጀመረዉን መልካም ተሞክሮ በጋራ ሆነን ለስኬታማነቱ እንድንረባረብ ኦዴፓ ጥሪዉን ያቀርባል፡፡

ኦዴፓ የሀገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች ትግል በማቀናጀት ወደ ድል እንዳሸጋገረ ሁሉ አሁንም ከእናንተ ተሳትፎ ውጪ የሚደረገው ትግል ግቡን ሊመታ እንደማይችል ያምናል፡፡

በቀጣይነትም ፓርቲያችን ከእናንተ ጋር በመሆን ጥቅምና ፍላጎታችሁን ለማስጠበቅ በግንባር ቀደምትነት ይታገላል፡፡

ለተከበራችሁ ምሁራንና የመንግስት ሰራተኞች!

በሀገሪቱ ዉስጥ እኩልነት ተረጋግጦ ውድድር በዕዉቀትና በሀሳብ ብቻ እንዲሆን እየተሰራ ባለበት የትግል ምዕራፍ ዉስጥ ወደ ፓርቲያችን በመቀላቀልም ሆነ በመደገፍ እያፈለቃችሁት ያላችሁት የበሰለ ሀሳብ ለዉጡን ለማሻገር የመሰረት ድንጋይ እየሆነ ነዉ ፡፡

ከህዝብና ከፓርቲያችሁ ከኦዴፓ ጋር በመሆን አዲስ ሀሳብ ማፍለቅና የትግል ታሪኩን በአቅጣጫ በጥናትና ምርምር በማሳየት የድርሻችሁን መወጣት ይጠበቅባችኋል፡፡

ኦዴፓ ለውጡን በዕዉቀት ላይ ተመስርተን እናሻግር በማለት ለምሁራን ጥሪዉን ያቀርባል፡፡

ህዝባችን ያለውን ቅሬታዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመሰረቱ ለመፍታት የመስሪያ ቤቶችን አደረጃጀት እና አሰራር በአዲስ መልክ ማደራጀታችን ይታወሳል፡፡

የተዘረጋዉ መዋቅር የህዝባችንን ችግር መፍታት የሚችለዉ መልካም ስነ ምግባርና ዕዉቀት ካለዉ የመንግስት ሰራተኛ ውጪ የሚታሰብ አይደለም፡፡

ስለሆነም እየታየ ያለዉ ለዉጥ ሰክኖ መቀጠል የሚችለዉ ለህዝባችን የተቀላጠፈና ተገቢ አገልግሎት በመስጠት የህዝብ እርካታን በማረጋገጥ ስለሆነ በተጠያቂነትና ወገናዊነት በተሰማራችሁበት የሥራ መስክ የዜግነትና የሙያ ግዴታችሁን በግንባር ቀደምትነት እንድትወጡ ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

ለተከበራችሁ የፀጥታ አካላት በሙሉ፤

ከህዝባችን ጋር በመሆን በሀገርና በክልላችን ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በተለያዩ ስፍራዎች መልካቸውን በመቀያየር በህዝባችን ላይ የሚቃጡ የትንኮሳ ሙከራዎችን ለማክሸፍ ርብርብ በማድረግ ላይ ትገኛላችሁ፡፡

ኪራይ ሰብሳቢዎች እየመጣ ያለዉን ለዉጥ ለማደናቀፍ በተደራጀ መንገድ የሚሰነዝሩትን ጥቃት በግንባር ቀደምትነት በመመከት ከዘመን ዘመን የማይረሳ ታሪካዊ መስዋትነት ከፍልችኋል፡፡

በሰራቹት ታሪካዊ ገድልም ይህንን የሽግግር ሂደት እየታደጋችሁት ትገኛላችሁ፡፡

በፈፀማችሁት አኩሪ ተግባርም የሀገራችንና የክልላችን የወደፊት ተስፋ እንዲቀጥል በማድረግ ህዝባችሁን ከአደጋ እየታደጋችሁት ነዉ ፡፡

በሀገርና በክልላችን ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ የዜጎች መብት ተከብሮ ሥርዓት አልበኝነት እንዳይኖር የህግ የበላይነት በአስተማማኝ መልኩ እንዲረጋገጥ የተሰጣችሁን ህዝባዊ አደራ ከህዝብ ጎን በመቆም በህዝባዊ ስሜት እንድትወጡ ኦዴፓ ጥሪዉን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶችና የትግል አጋር ድርጅቶቻችን!

ድርጅታችን ኢህአዴግ በሀገራችን ህዝቦች ላይ ተጭኖ የነበረዉን ጭቆና በመገርሰስ አስተማማኝ ድሎችን ማስመዝገብ የጀመረዉ የዉስጥ ችግሩን በመፈተሸና በመፍታት ነዉ፡፡

ሀገራችን እንደ ሀገር መቀጠል የምትችለዉ ከትላንትናዉ አካሄድ በመማር የህዝባችንን ፍላጎትና ጥቅም እያከበርንለት እና በህግና በህግ አግባብ በመፍታት ከሄድን ብቻ ነዉ፡፡

እኛ ስንደማመጥ ለህዝባችን ምሳሌ እንሆናልን፡፡ እኛ በሀሳብ ሳንግባባ ስንቀር ለህዝባችን ችግር እንሆናለን፡፡ ስለሆነም ከሁሉም አስቀድመን የህዝባችንን ፍላጎት በማስቀደም በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመመካከር ለሀገር ግንባታ በጋራ እንስራ፡፡

የተከበራችሁ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በሙሉ!

በብዝሃነት ላይ ለተመሠረተችዉ ሀገራችን የዴሞክራሲ ጉዳይ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ስለሆነም ያለዉን የፍላጎትና የሀሳብ ልዩነት እና አሰራር እኩል በሆነ መልኩ ማስተናገድ መቻል ይኖርብናል፡፡

በሰፋዉ የፖለቲካ ምህዳር በመጠቀም ቀጣይነት ያለዉ ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርሻ ከፍተኛ ነዉ፡፡

በተለይም በሽግግር ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችና እንቅፋቶችን በመመከት የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች መደማመጥ ወሳኝ ስለሆነ በምናደርገዉ ማንኛዉም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዉስጥ የህዝቡን ተጠቃሚነት በማስቀደም፣ ህግና ስርዓትን በማክበር፣ በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንድትታገሉ ጥሪያችንን አጥብቀን እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ የኦዴፓ አባላት! ፓርቲያችን ኦዴፓ አያሌ ድሎችን በማስመዝገብና የፓርቲዉን ዉስጣዊ ችግሮች በማጥራትና ወድቆ እንዲነሳ፣ ተነስቶም ራሱን በማደስ ተዓምር እንዲሰራ ዉስጣዊ ትግል በማካሄዳችሁ በፓርቲዉ ዉስጥ ለታየዉ ለዉጥ መተኪያ የሌለዉ ድርሻ ተወጥታችኋል፡፡

ከጠንካራ ፓርቲ በስተጀርባ ጠንካራ አባላት እንዳሉ አስመስክራችኋል፡፡  ኦዴፓ በአሁኑ ወቅት የተረከበዉን ታሪካዊ ሀላፊነት እንዲወጣ ዛሬም እንደትላንቱ ግንባር ቀደም ተሳትፎአችሁ ወሳኝ ነዉ፡፡

ህዝባችን ደረጃ በደረጃ እያካሄደ በሚገኘዉ ትግል ዉስጥ በመሳተፍና በመምራት ያሉትን ችግሮች ለመፍታትም ከፍተኛ ሀላፊነት አለባችሁ፡፡

ጊዜዉ የሚጠይቀዉን የትግል መድረክ በመቅደም ለፓርቲዉ ዓላማ በመሰዋት በተሰማራችሁበት የስራ መስክ ሁሉ ግንባር ቀደም በመሆን የህዝባችንን ጥያቄዎች በአሰቸኳይ በመመለስ አንድነትና ጓዳዊ ስሜትን ከመቼዉም ጊዜ በበለጠ በማጠናከር እኛን ለመስበር የሚቃጣዉን ጥቃት በዕዉቀት እና በማስተዋል ላይ በተመሰረተ ለዉጡን እንድናሻግር ፓርቲያችሁ ጥሪ ያቀርብላችኋል፡፡

ኦዴፓ የኢትዮጵን አንድነት፣ ሀገራዊ ክብር፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከመቼዉም ጊዜ በበለጠ ጠንክሮ ይሰራል!

የኦዴፓ ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት

መጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ.ም

ፊንፊኔ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም