ኦዴፓ ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል- የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ

90

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2011 ማንኛውም ዜጋ በእኩልነት የሚኖርባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በትኩረት ይሰራል ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

ሊቀመንበሩ ኢትዮጵያውያን  'የኔ ነው' ከሚል መገፋፋት ወጥተው 'የእኛ' ነው ወደሚል አብሮነት እንዲሸጋገሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ዶክተር አብይ አህመድ ይህን ያሉት የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን  29ኛ ዓመት የምስረታ በዓልና 1ኛ ዓመት የለውጥ ጉዞን ባከበሩበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤  "እየተከበረ ያለው የፓርቲው 29ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ በእኩልነት ለመኖር ያደረገው ትግል ወደ ተሻለ ምዕራፍ መሸጋገሩን ያበስራል" ብለዋል።

ኢትዮጵያን እንደ ድንኳን፤ ህዝቦቿን ደግሞ ድንኳኑን እንዳቆሙት ምሰሶዎች በመመሰል ያለውን የአብሮነትን ፋይዳ ያብራሩት ሊቀመንበሩ፤ ከዚህ አንጻር ፓርቲያቸው ሁሉም ዜጋ የሚኮራባትን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከመቸውም ጊዜ በላይ አበክሮ እንደሚሰራ አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ህዝቦችን የቆየ አብሮነት ለመለያያት የሚሰሩ አካላት መበራከታቸውን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ህብረተሰቡ እነዚህን መከተል እንደማይገባም አሳስበዋል።

ለአብነትም የጉጂ ኦሮሞንና የጌዲኦ ማህበረሰብን እንደ መነሻ በመጠቀም ዜጎች እንዲለያዩ በማህበራዊ ሚዲያ ተደብቀው የሚሰሩ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ "ነገር ግን ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ኢትዮጵያዊ ሆነው ከመቀጠል የሚያቆማቸው አይኖርም"  ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ አበባን በሚመለከት የሚነሳውን ሃሳብ ሲገልጹም "አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ነቀምትም ሆኑ ሌሎች ከተሞች የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው" ብለዋል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኦዲፒ ከሌሎች የለውጥ ሃይሎች ጋር ሆኖ  በኢትዮጵያ ለመጣው ለውጥ ያበረከተው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል።

ለውጡ ዓለም የተደመመበት ስኬቶች የተመዘገቡበት እንደሆነም ጠቁመዋል።

ለውጡን የሚፈትኑ ተግዳሮቶች ሊያስፈሩን ሳይሆን፤ ቀበቷችንን ጠበቅ አድርገን የበለጠ እንድንሰራ የሚያተጉን መሆን አለባቸውም ብለዋል።

በየደረጃው የሚገጥሙ ፈተናዎችን በድል ለመወጣት አመራሩ በተግባር ፋና ወጊ ሆኖ ተባብሮ መሰራት አንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል አቶ ደመቀ።

በአሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅትነት ከተመሰረተ 28ኛ ዓመቱን በታላቅ አገራዊ ለውጥ ውስጥ ባለፈው ዓመት ያከበረው ኦዴፓ፤ መጠሪያውን ወደ አሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲነት መለወጡ ይታወሳል።

ፓርቲው 29ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉንና 1ኛ ዓመት የለውጥ ጉዞን አስመልክቶ ትናንት ባወጣው መግለጫም መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከኦሮሞ ወንድሙ ጋር ሆነው የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠልና ለአገር ግንባታ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪውን አቅርቧል፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም