በተሽከርካሪ አደጋ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ በሌሎች ስድስት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደረሰ

58

ሐረር መጋቢት 17/2011 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሐረማያ ወረዳ ዛሬ ጠዋት በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ በሌሎች ስድስት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዲቪዝን ኃላፊ ኮማንደር ስዩም ደገፋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት አደጋው ዛሬ ጠዋት የደረሰው ሁለት ተሽከርካሪዎች በመጋጨታቸው ነው።

ከውጫሌ ድሬዳዋ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ 3- 68359 ኢት የሆነ የጭነት መኪና ከድሬዳዋ ቆቦ ይጓዝ የነበረና የሰሌዳ ቁጥር (3) - 65201 አ.አ የሆነ ሚነባስ ተሽከርካሪ ገጭቶ ከመንገድ ውጭ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ በመክተቱ አደጋው ሊከሰት ችሏል።

ኮማንደር ስዩም እንዳሉት አደጋው የደረሰው በወረዳው ደንገጎ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በተለምዶ ቢሻን ዲልዲላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

በአደጋውም የሁለቱ መኪኖች አሽከርካሪዎችን ጨምሮ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ በሌሎች 6 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም በድሬዳዋ ድልጮራ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው የሞቱትን ሰዎች አስክሬን ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ከሆስፒታሉ መረከባቸውን ተናግረዋል።

እንደ ኮማንደር ስዩም ገላጻ  የአደጋውን መንስኤ ለጊዜው ባለመታወቁ ፖሊስ እያጣራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም