በትግራይ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚውል የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚውል የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ተገኘ
መቀሌ መጋቢት 17/2011 በትግራይ ክልል ለሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች የሚውል 400ሺህ ብር ግምት ያላቸው የትምህርት ቁሳቁሶችና የገንዘብ ድጋፍ ተገኘ፡፡
የትምህርት ቁሳቁሶቹ ድጋፍ የተገኘው ከአዲስ አበባ የትግራይ ወጣቶች ማህበር አባላት እንዲሁም 80ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ደግሞ በመቀሌ ኢንተሌክችዋል ከተባለ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን ነው፡፡
እነዚህን የመጽሐፍት ፣የደብተር ፣የመጻፊያ ቁሳቁሶችና ገንዘቡን የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ትናንት ተረክቧል፡፡
በአዲስ አበባ የትግራይ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ሰለሞን ገብሩ ድጋፍ ካበረከተ በኋላ ተፈናቃይ ወገኖችን ለመርዳት የጀመረቱን ድጋፍ እንደሚቀጥሉበት ገልጿል፡፡
የኢንተለክችዋል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕስ መምህር ሚስተር አርጀን ዘካሪያ በበኩላቸው የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ያዋጣው እና ከተለያዩ ዝግጅቶች ያሰበሰበው ገንዘብ ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲውል ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡
የወጣት ማህበሩ አባላትና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ የተቸገሩትን ተፈናቃይ ወገኖችን ለመርዳት በራሳቸው ተነሳሽነት ላደረጉት ድጋፍ የሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ኪሮስ ሐጎስ በክልሉ መንግስትና በተፈናቀዮች ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በነበረው የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ከ89ሺህ በላይ ወገኖች በክልሉ እንደሚገኙ ጠቅሰው የድጋፍ አሰባሳቢ ቦርድ ተቋቁሞ ሃብት እየተሰባሰበ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡