ሸካና ኮቦ

554

ጥላሁን አያሌው /ከሚዛን -ኢዜአ/

ጠዋት ማልዶ ዕለቱ ሲወግግ ከሚዛን እንብርት እሽክርክሪቱን የጀመረው የጉዞ መኪናችን ንጋቱን ገስግሶ ፀሐይ ሳትከረዝዝ ቴፒ ከተማ አደረሰን፡፡

ሚዛን እና ቴፒ በሃምሳ ኪሎሜትር የሚራራቁ ጎረቤትማማች ከተሞች ናቸው፡፡እነዚህ እህትማማች ከተሞችም በብዙው ተመሳስሎሽ አላቸው፡፡

ሁለቱም ደንን ተጎናጽፈው የተከናነቡ የተፈጥሮ ሀብት ሃብታሞች ናቸው፡፡ዙሪያ ገባቸው የለመለመ አረንጓዴ ለበስ ውብና ማራኪ ስንዱ ከተሞች፡፡ ይህ አማዞናዊ ገጸ መልካቸውም  የወል ባህሪያቸው ነው፡፡

በቅርብ እርቀት የከተሙት ሚዛንና ቴፒ ከተፈጥሮ ጸጋቸው በጎንዮሽ ሕብራዊነታቸው ሌላ መለዮ መልካቸው ነው፡፡ማህደረ ብዙኃንነታቸውም ሚዛንና ቴፒን አንድም ሁለትም ያደርጋቸዋል፡፡

በወቅት ቴፒ እንደደረስኩ ጊዜ አላበከንኩም ። ወዲያው ከካሜራ ባለሙያችን ጋር ፈጥነን ወደ ቴፒ መነኸሪያ ተጓዝን፡፡

የቴፒ መነኸሪያ ተጨናንቃ ሥራ በዝቶባት ነው ያገኘኋት፡፡ ያላቅሟ ሰው በብዛት ለማስተናገድ ተገዳለች፡፡

የመናኸሪያው ተስተናጋጅም በጠባቡ በር እየተጋፋ ይወጣል፤ይገባል፡፡ ወቅቱ የበዓል ሰሞን መሆኑ ደግሞ ከወትሮው በላቀ መንገደኛው እንዲበራከት ምክንያት ሆኗል፡፡

ከቴፒ መናኸሪያ መነሻቸውን ያደረጉ ተሽከርካሪዎችም ወደሚዛን፣ጅማ፣ ማሻ፣ሜጢ፣አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች  የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ይበተናሉ ፡፡ ከየአቅጣጫዎቹም ተጉዘው የሚመጡ ተሸከርካሪዎችም ጠባቧ የቴፒ መናኸሪያ ውስጥ ያርፋሉ፡፡

የመኪናው ጥሩንባ፤የረዳቶች ጥሪ፤የተጓዡ ውክቢያ ሁሉም አንድ ላይ ይጮሀሉ፤አንድ ላይም ይሰማል፡፡ዝብርቅርቅ ያለድምጽ፤ውጥንቅጡ የወጣ ጩኸት፡፡

የሚስተዋለው ሁነትም በአንድ የምስባክ ጉባዔ ላይ በተዓብዮ ምክንያት በኃጢያታቸውም  መብዛት ቋንቋቸው የተዘበራረቀባቸው የባቢሎናውያን ታሪክ  አስታወሰኝ፡፡

ያም ሆኖ ግን አንዳችም ከመግባባት አያግዳቸውም፡፡ተፈላላጊዎች ያላንዳች ችግር ሀሳብ ለሀሳብ ይገናኛሉ፡፡በሩምታው ውስጥ መደማመጥ፤በብዥታው መሀልም መግባባት አለ፡፡

እኛም ትርምሱ አላገደንም ወደመዳረሻችን የሚያደርሰንን መኪና አግኝተናል፡፡መጓጓዣችን ሊሞላ አካባቢ ስለደረስንም ብዙ አልተጉላላንም፡፡በረዳታችን ውትወታና ብርቱ ጥረት በሩቅም በቅርብም ያሉ የጉዞአችን አባላት ተከተቱና ጉዞ ተጀመረ፡፡

ቅጥቅጥ መለስተኛ የህዝብ ማላለሻ መኪናችን ከተፈቀደለት የመጫን ልክ በላይ ውስን ሰዎችን አክሏል፡፡ሰዓቱ ገና ጠዋት ቢሆንም ከተሳፋሪው መበራከት ጋር ተዳምሮ አየሩ መሞቅ ጀምሯል፡፡የታመቀው አየርም እየቆየ መወበቅ ይዟል፡፡

በእርግርጥ ቴፒ በባህሪዋ ሞቃት ከተማ ናት፡፡ከተማዋ ምንምእንኳን ዙሪያዋን በደን ያጌጠች አረንጓዴ   ገነት  ብትሆንም ቴፒ ተኳሳ ናት – ወበቃም ከተማ፡፡

መነሻችን ስለንግድ እንቅስቃሴዋ በአያሌው የሚወራላት መልከ ጉራማይሊት ደማቋ ቴፒ ስትሆን፤የጉዟችን መዳረሻ በአንጻሩ የዞኑ ዋና ከተማ የሆነችው ማሻ ናት፡፡ከቴፒ ማሻ ለመድረስ 87 ኪሜ ከፊት ለፊታችን ይጠብቀናል፡፡

ምቹውን የቴፒ ከተማ መልከዓ ምድርን እያጋመስን 20 ደቂቃዎች የማይበልጥ ከተጓዝን በኋላ እርምጭ የሚባል ቀበሌ ስንደርስ አንድ ትልቅ አረንጓዴ ቅብ ታፔላ ታየኝ፡፡

ታፔላው  በአንድ ክፍሉ በአረንጓዴ የተሸፈነ ምድር፤ቀሪ አካሉ ደግሞ የተንጣለለ ሰፊ ሐይቅ፤በሐይቁ ላይም በከፍታ አዕዋፋት ሲረብቡና ሲከንፉ ተስለውበታል፡፡

በአረንጓዴው መደብ ላይ በዓለም የሣይንስ የትምህርትና ባህል ቅርስነት የተመዘገበው የሸካ ጥብቅ ደን መሆኑን የሚነግር ጽሑፍ ተከትቧል፡፡የድርጅቱን መለያና ተባባሪ አጋር ተቋማት አርማም አራት በአራት በተሰራው ማዕቀፍ ህዳጉ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

ምስሉም ጥሩ የንድፍ ሙያተኛ የጥበብ ሰው የተጠበበት ስለመሆኑ ያሳብቃል፡፡ቅንብሩም ስሜት ነክ ቀልብ ሳቢ ነው፡፡በበኩሌ አሞግሸዋለሁ፡፡

በመስኮት በኩል መሆኔ በየደረስንበት የዓይን ቀለብ የሆኑ ሁነቶችን እንዳሻኝ እንዲኮመኩም ዕድል ፈጥሮልኛል፡፡ስሜቴን ገዝቼ ትዝብቴን እየከተብኩ ነው፡፡

ታፔላው ከቆመበት ጀምሮ ግራና ቀኛችንን በደን ተውጠን በረጃጅም ዛፎች መሀል እያጋመስን ጉዟችን ወደመዳረሻችን ቀጥሏል፡፡የመሂናችን ዘዋሪም ከቀልቡ ሆኖ እየመረሸ ነው፡፡

ከከባቢው ተፈጥሯዊ ሁነት ጋር ስምሙ የሆኑ ጆሮ ገብ ሙዚቃዎችን እያስደመጠን ስለሆነም መላችንን አስደስቶናል፡፡

የአስቴር አወቀ ልስልስ የፍቅር ዜማዎች፤የኤፍሬም ታምሩ ጋራ ሸንተረሩን ጨምሮ የአንጋፋ ድምጻውያን ጣዕመ ዜማዎች ከተሸከርካሪው ጣሪያ እየተፈራረቁ ይደመጣሉ፡፡

የሙዚቃው ጉልበት ተጽዕኖ አሳድሮብን መሰለኝ አርምሞ ነግሷል፡፡

በቦርሳችን የያዝንው  ውህድ ጣፋጭ የፍራፍሬ ጭማቂ እየመጠጥን፤ከጉዟችን ባሻገር ድንቅ ተፈጥሮ ጸጋ እየኮመኮምን፤እያደር አዲስ የሆኑ ቃናቸው የሚጥሙ ለዛ ያላቸው ዜማዎች እያጣጠን ጉዟችንን ቀጥለናል፡፡በግሌ እያየሁት ባለሁት ድንቅ ተፈጥሮ እጅጉን ተደስቻሁ፡፡ቀናዒ ጉዞ፡፡

ጉዟችን እየገፋ በሄደ ቁጥርም የሚታየው ትዕይንትም በዓይነቱ በብዛቱም እየበዛ ነው፡፡ትንሽ እልፍ ባልን ቁጥርም አዕላፍ የተፈጥሮ በረከት ይገጥመል፡፡

በረጃጅም ዛፎች መካከል በተቀደደ አውራ ጎዳና ውስጥ ለውስጥ እየተሸሎከሎክን ነው እየተጓዝን ያለንው፡፡ዛፎቹ  ዕድሜ ጠገብ ከመሆናቸው የተነሳም አብዛኞቹ ጺማሞች ናቸው፡፡አንዳንዶቹ ዕድሜ ጠገብ ዛፎችም ግንዳቸው ጸጉሯል፡፡ከፊሎቹ ተጠላልፈውና ተቆላልፈው ገሚሶቹ ተደጋግፈው አንዱ በሌላው ውስጥ በቅሎ ይታያሉ፡፡ተክሎች ሕብር ሰርተው ይታያሉ፡፡

በጺማሞቹ ሰማይ ጠቀስ ዛፎች አናት ላይ እንደልባቸው የሚቦርቁ ጉሬዛዎች ሌላኞቹ የደኑ ሲሳዮች ናቸው፡፡ጉሬዛዎቹ በራሰቸው ርስት ተፈጥሮ በለገሰቻቸው መስካቸው ሕይወትን ያጣጥሙ ይዘዋል፡፡

መልከኞቹ ጉሬዛዎች ከአላፊ አግዳሚው ጋር አየውህ አላየውህ ድብብቆሽ ይጫወታሉ፡፡ከአንዱ ዛፍ ወደሌላኛው ያለክንፍ ሲከንፉ የጉድ ናቸው፡፡

እኒህ ውብ እንስሳት በሕብር ሲዘምሩ ለሰማቸው ደግሞ ሀቅል ያስታሉ፡፡ድምጸታቸው ስልተ ምትን ጠብቆ በቅላጼ እንጂ እንደነገሩ እንደመጣ አይጮሁም፡፡የጉሬዛ ዝማሬ ጉሮሮ ላይ ነው፡፡እንደማንቋረር አይነት፡፡ከሽልሞቹ ጉሬዛዎች ላንቃም ወፍራም የተገራ ድምጸት እየተቆራረጠ ሲወጣና ሲደመጥ ስሜት አለው፡፡

ጉሬዛዎች ተንኮንል አያውቁም፡፡ሕሊናቸው እንደመልካቸው ቀና ነው፡፡በተለምዶ ጉሬዛዎች ሰዓት አክባሪ ናቸው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ኧረ እንደውም ለፈጣሪያቸው ተገዥና ጾመኞች እንደሆኑም ተነግሮኛል፡፡

ውቦቹ ጉሬዛዎች ንጋት ላይ ሰዓት ጠብቀው ይዘምራሉ፤ምሳ ሰዓት ሲደርስም የራሳቸው ጉሬዛዊ ዜማ አላቸው፤አመሻሽ ሲሆንም በሕብረት ዘምረው ነው ወደማህደራቸው የሚገቡት፡፡

የሸካ ምድር ዓይን ባረፈበት ሁሉ የውበት ስበት የማይጠፋበት ነው፡፡ከዳገት የሚንፏፉ ፏፏቴዎች በቅርብ ርቀት ይታያሉ፡፡የጥብቅ ደኑ ውጤት የሆኑት ፏፏቴዎችም ሌለኞቹ ማራኪ ገጽታዎች ናቸው፡፡ከገመገሙ ቁልቁል ሲበተኑ የሚታዩት ፏፋቴዎች ዳገት ላይ የተሰጣ ነጭ ሻሽ ይመስላሉ፡፡

የጉዞ ፌርማታዎቻችን ደግሞ ትንንሽ ኩሬዎች ናቸው፡፡አንዱን ተሻግረን ሌላ የሚፍለቀለቅ ምንጭ ይገኛል፡፡በየግንዱ ሥር በየረባዳው ቦታ ሁሉ አነስተኛ ወንዞች አይታጡም፡፡ምድሩ ሁሉ የወረዛ ነው፡፡

ይህ ጥብቅና ጥቅጥቅ ደን ውስጡ ዘንባባ፤ቀርከሃ፤ዋንዛ፤ዋርካ፤መንደሪን፤እንጆሪ፤ግራዋ የማውቃቸውና ማላውቃቸውን ጨምሮ ልዩ ልዩ የተክል ዓይነቶች አቅፎ ይዟል፡፡ደኑ ባለው ብዝሃ ተፈጥሮ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ማግኘቱ አግባብነትምም ተገቢነት አለው፡፡

በዚህ ሁናቴ ማሻ ወረዳ ቤቶ ቀበሌ ደርሰናል፡፡ማሻና አካባቢዋ እርጥበት አዘል ቃል አይገልጻትም፡፡ማሻ ነፋሷ እርጥብ ነው፡፡በተለይም ንጋት ረፋድና እንዲሁም ጀምበር ስታዘቀዝቅ ቅዝቃዜው የጉድ ነው፡፡ብርዱ ያንሰለስላል፡፡

እዚህ ላይ አካባቢው ብሉያዊ ሥነ ምህዳሩን ጠብቆ ሊቆይ የቻለበትን መሰረታዊ ምክንያት መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡

ይህ ድልብ ተፈጥሮን የመጠበቅ ይትብሀል እንዴት ሊዳብር ቻለ ለማለት እንገደዳለን፡፡ተፈጥሮ ሀብትና ማህበረሰቡስ  ምንና ምን ናቸው ዝምድናቸውስ  

አቶ ግርማ ጌዴኖ የአካባቢው ነዋሪ ሲሆኑ ለነዚህ ጥያቂያችን ምላሽ አላቸው፡፡አቶ ግርማ በዚሁ የሻኪቾዎችን ባህልና ወግ እየማጉ ያደጉ ጉምቱ የባህል ሰው ናቸው፡፡

በሻኪቾ ብረሰብ ኮቦ የተሰኘ ባህል አለ፡፡የአካባቢያችን ህያውነትም ምስጢሩ ኮቦ ነው ይላሉ፡፡ኮቦ በሸካዎች ዘንድ ባህላዊ የደን ሀብት አጠባበቅ ሣይንስ ነው ሲሉም ይገልጹታል፡፡

አቶ ግርማ እንደሚሉትም ደን ለሸካ ማህበረሰብ ህልውናው ነው፤ሸካ ለተፈጥሮ ተፈጥሮም ለሸካ ይኖራሉ፤ይህ ለደን የሚሰጥ እንክብካቤም የቆየና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልምድ ነው፡፡

ህብረተሰቡ በብዛት ማር የማምረት ልምድ አለው፡፡ማር የሚመረተው ደግሞ ደን ሲኖር መሆኑ እሙን ነው፡፡ህብረተሰቡ ደንን እንደሀብቱም እንደህልውናውም ይቆጥረዋል፡፡

ሸካዎች ደንን የሚጠብቁትና የሚንከባከቡት ለንብ ማነብ ብቻ ሣይሆን ከደን ውስጥ ኮረሪማ፤ቡና፤ዝንጅብልና ተለያዩ ምርቶችን ለማግኘትም ጭምር ነው፡፡በጥምር ግብርና በሚያገኙት ተጨማሪ ሀብትም ገቢያቸውን ይደጉሙበታል፡፡

ታዲያ ይህንን የመሰለ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያገኛቸው የደን ሀብትን በዘላቂነትም በአስተማማኝ ሁኔታም ለመጠበቅ የሚያስችላቸው ኮቦ የተሰኘ ባህላዊ ዘዴ ፈልስመዋል፡፡

አቶ ግርማ የኮቦን ስልተ አሰራርን እንዲህ ያብራሩታል፡-ሰፊ የደን አካባቢዎችን ንብ አናቢ ማር አምራች አርሶ አደሮች በምድብ በምድብ ይከፋፈላሉ፡፡  ለምሳሌ አንድን የደን ቀጠና እስከ አንድ መቶና ከዚያም በላይ ሰዎች ሊከፋፈሉት ይችላሉ፡፡

እንደዚህ ያሉ የወል/የጋራ የደን አካባቢዎችም ከነሙሉ ኃላፊነት ለእያንዳንዱ ነዋሪ  ይሰጣሉ፡፡

ከደኑ ንብ ለማነብ ኮረሪማ ለማልማትና ሌሎችም ጥቅሞችን ለማግኘት የተረከቡ ግለሰቦችም ተጠያቂነትም ጭምር አለባቸው፡፡

ሁሉም ንብ አናቢ የተሰጠውን የማር ይዞታ በጥንቃቄ የመያዝና ደኑን የመንከባከብ ሙሉ ኃላፊነት ይጣልበታል፡፡ማንኛውም አርሶ አደር ከተፈቀደለት የደን ክልል ውጭ መጠቀም አይችልም፡፡በደኑ ውስጥም ማምረት የሚፈቀድለትም ማርና ቅመማ ቅመም ብቻ ነው፤በይዞታነት የባለቤትነት መብት የለውም፡፡

በዚህ ማህላዊ ባህላዊ አሰራር መሰረትም በኃላፊነት ደኑን ከተረከበ በኋላ ዛፍ የቆረጠና በደኑ ላይ አንዳች  ጉዳት ያደረሰ፤ጉዳት ያስደረሰና ደን ሲጨፈጨፍ አይቶ ዝም ያለ ያላጋለጠ ሁሉም ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡

በባህላዊ የኮቦ አሰራር መሰረትም ጥፋተኞች እንደጥፋታቸው መጠን ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡በተጨማሪም ደኑ ላይ አላግባብ ጥፋት ያደረሰ ግለሰብም በቀጣይ ከኮቦ አባልነት ይሰናበታል፡፡ከኮምቦ የሚያገነው ጥቅም ይቀርበታል ማለት ነው፡፡

ደንን በጠበቅ የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ ጉዳይ ሣይሆን የሁሉም ማህበረሰብ አባል ኃላፊነት ጭምር ነው፡፡ሁሉም የማህበረሰብ አባል ደንን ከችግኝ ተከላ ጀምሮ ጸድቆ ዛፍ እስኪሆን ተክልን መንከባከብ የውዴታ ግዴታው ነው፡፡

አቶ ግርማ እንደሚሉትም ኮቦ የተሰኘው ባህላዊ የደን አጠባበቅ ልምዳችንም አካባቢያችን በድርቅ እንዳይጎዳና በዝናብ እጦት ለረሀብና ለችግር ሳንዳረግ እንድንኖርም አስችሎናል፡፡አካባቢያችንም ዓመት ሙሉ እንደወዛ ይዘልቃል፡፡

ሌላኛው የዚህ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ብርሀኑ ሻረፎ በበኩላቸው የደንን ፋይዳ በሚያገኙት ጥቅም ይገልጹታል፡፡

ደን እንጀራቸው፤ዛፍ ጧሪያቸው ተፈጥሮ ሕይወታቸው መሆኑን አበክረው ይናገራሉ፡፡

በኮቦ ባህል ተሸንሽኖ በደረሳቸው ደን ውስጥ እስከ  አንድ መቶ ሃምሳ ባህላዊ ቀፎ እንዳላቸው ነግረውኛል፡፡በባህላዊ መንገድ ከሚያመርቱት የማር ምርትም በአመት እስከ ——–   ኪሎ ግራም ምርት እንሚያገኙም ጭምር፡፡

ንብ አንቤ፤ማር አምርቼ በማገኘው ገንዘብም ልጆቼን አስተምራለሁ፤ሕይወቴን እመራበታለሁ ብለዋል፡፡

እኔን ጨምሮ የአካባቢያችን ሰዎች በዚህ መልኩ በተንከባከብንው ልክ ደን ዋጋችንን ይከፍለናል ነው ያሉት፡፡

የዚህ ሁሉ ጥቅም መሠረቱ ከአባቶቻችን በልምድ የወረስንው ኮቦ ነው የሚሉት አቶ ብርሀኑ፤ኮቦን አጥብቀን የምንከባከበው ህልውናችን የመኖራችን መሠረት ስለሆነ ነው ሲሉም ጥቅምና ፋይዳውን  ያብራራሉ፡፡

በዞኑ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ ሰዎች በዚህ መልክ ለዘመናት ሲጠቀሙ ኖረዋል፡፡ኮቦንም በአደራ ከቀዳሚዎቻቸው ተረክበዋል፤የአባቶቻቸውን ዕሴት ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት መመህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዘውዴ ካሳ  በሸካ ዞንና አካባቢው በብዝሀ ሕይወት ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ናቸው፡፡

አካባቢው ሰፋት ያለው የብዝሀሕይወት የሚገኝበት መሆኑንና፤ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉ የዕጽዋት ዝርያዎችን ያቀፈ መሆኑንም ዶክተር ዘውዴ ይናገራሉ፡፡

በመጥፋት ላይ ያሉና ሌሎች አካባቢዎች የሌሉ የዕጽዋት ዓይነቶች ስለሚገኙበት የበለጠ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ማህበረሰቡ በሀገረበቀል ዕውቀት ታግዞ እስከ አሁን ያቆየውን የደን ሀብት ጥበቃና አያያዝ ዘዴ ማጠናከርና ለሌሎችም እንዲተርፍ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ሕይወታቸው ከአካባቢ ልማት ጋር ቁርኝት ያለውና ለደን አጠባበቅ ልዩ ትኩረት ለሚሰጡ ማህበረሰቦችም የማበረታቻ ድጋፍ ዕውቅና በመስጠት አካባቢውን በበለጠ እንዲጠበቅ ያስችላል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዓለማችን ከሚፈታተኗት ዋነኛ ተግዳሮቶች መከካል አንዱ የአየር ንብረት መዛባት ነው፡፡ነገር ግን ይህ ዓለም ስጋት ሸካዎችን አላያቸውም፡፡እነሱም አያውቁትም፡፡

የሸካ ማህበረሰብ በኮምቦ ባህላዊ የደን አጠባበቅ ሣይንሱ አካባቢው ተፈጥሯዊ ይዘቱን እንደተበቀ ለአየር ንብረት ለውጥ ሳይጋለጥ ማቆየት አስችሏል፡፡

ሌሎች አካባዎችም እንደሸካዎች ሁሉ በተለያዩ ከባቢያዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች መነሻ ተፈጥሮን ቢጠብቁ የተጎዳውን ሥነ ምህዳር ዳግም እንዲያገግም ማድረግ ይቻላል፡፡

ከመልሶ ማልማት ጎን ለጎን ግን በሀገሪቱ አንዳንድ አካባዎች የሚገኙ ቅሪት የደን ሀብቶችን ባሉበት ተጠብቀው እንዲቆዩ ማድረግ የተሻለው አማራጭ ነው፡፡

በዋናነትም በደቡብ ምዕራብ ሸካ፤ካፋና ቤንች ማጂ ዞኖች ከፍተኛ የደን ሽፋን የሚገኝበት የሀገራችን ክፍል በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡

ሌላው ይህንን ተፈጥሮ ጠብቀውና ተንከባክበው ላቆዩ ማህበረሰቦች ዕውቅና በመስጠትና በማበረታታት አርዓያ ማድረግ ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡

ኮቦ ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችል  ተግባር ነው፡፡ሌሎች የሀገራችን ማህበረሰቦች በዓርዓያነት እንዲጎበኙትም ዕድል ሊመቻች ይገባል፡፡

የዘርፉ የምርምር ምሁራንና ተቋማትም ሩቅ ከሚያማትሩና በማይተገበር ንድፈ ሀሳብ ጊዜ ከሚያባክኑ ዙሪያቸውን ቢቃኙ ጓዳቸውን ቢፈትሹ እልፍ ጠቃሚ ግኝቶችን ማበርከት ይችላሉ ባይ ነኝ፡፡

ደንና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንም በማስተማሪያነት ሊጠቀመው የሚችልበት መልካም አጋጣሚም ይመስለኛል፡፡

          ቸር እንሰንብት!!!