የበልግ አብቃይ በሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ዝናብ ይጠበቃል

82

አዲስ አበባ  መጋቢት 17/2011 በኢትዮጵያ በመጪዎቹ አስር ቀናት አብዛኛዎቹን የበልግ አብቃይና ተጠቃሚ ቦታዎችን ባካተተ መልክ በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተሻለ ዝናብ እንደሚጠበቅ ብሄራዊ የሚቲሪዮሎጂ አገልግሎት አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ በመጪዎቹ አስር ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ እና ምእራብ ወለጋ" ጅማ" ኢሉአባቦራ ምዕራብና ሰሜን ሸዋ" አዲስ አበባ! ከአማራ ክልል ደግሞ ሰሜንና ደቡብ ወሎ" ዋግህምራ" ሰሜን ሸዋ እንዲሁም ምሥራቅ ጎጃም ዝናብ ያገኛሉ።

የምሥራቅና የደቡብ ትግራይ ዞኖች! ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደግሞ የሀድያና የጉራጌ ዞኖች" የከፋና የቤንች ማጂ" የወላይታ" የዳውሮ" የጋሞጎፋ ዞኖች በአንዳንድ ቦታዎቻቸው ላይ ዝናብ እንደሚጠበቅም ተመልክቷል።

የምሥራቅ አማራ አጎራባች የሆኑት የአፋር ክልል ዞኖች" የደቡብ ጎንደር" የጋምቤላ ክልል ዞኖች" የምዕራብና የምሥራቅ ሐረርጌ! አርሲና ባሌ በጥቂት ሥፍራዎቻቸው ላይ ዝናብ ይኖራቸዋል$  የተቀሩት የሀገሪቱ አካባቢዎች በአመዛኙ ደረቅ ሆነው ይሰነብታሉ።

የሚጠበቀው ዝናብ በተለይም ለበልግ አብቃይ አካባቢዎች ለበልግ እርሻ ሥራዎች፣ ለአፈር እርጥበት መጠናከርና ለቋሚ ተክሎች የውኃ ፍላጎት መሟላት እንዲሁም የረጅም ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራት፣ ለእንሰሳት የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ለአረንጓዴ ተክሎች ልምላሜና ለጓሮ አትክልት እንዲሁም ለከብቶች የመኖ አቅርቦት ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ኤጀነሲው አመልክቷል።

በመሆኑም በተለይም በሰሜን ምሥራቅ የሚገኙ ውኃ አጠር የሆኑ አካባቢዎች የሚገኘውን የዝናብ ውኃ ለመሰብሰብና ለማጠራቀም የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።

በመሆኑም አርሶ አደሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ውኃን የመሰብሰብና የማጠራቀም ተግባራት በማጠናከር በመካከል ለሚገጥሙ ደረቅ ሰሞናት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የተለያየ ውሀ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን መጠቀም የሚገባ መሆኑን እንመክራለን፡፡

በሌላም በኩል በመደበኛ ሁኔታ በዚህ ጊዜ እርጥበት ማግኘት የሚጀምሩት በደቡብና በደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚጠበቀው ደረቅ ሁኔታ በደጋማው አካባቢ ለሚዘሩ ሰብሎችም ሆነ በአካባቢው ለሚካሄደው አርብቶ አደር አካባቢዎች ለእንስሳት የግጦሽና የመጠጥ ውሀ አቅርቦትን ከማግኘት አንጻር አሉታዊ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም በአንዳንድ በሰሜን ምስራቅና በምስራቅ ኦሮሚያ አነዲሁም በአርሲና ባሌ ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ከሚጠበቀው አነስተኛ ዝናብ አንጻር እርጥበት አጠርና ከፍተኛ የውኃ ትነት ያለባቸው አካባቢዎች የውኃን ብክነትን ለመከላከል የሚያሰችሉ ዘዴዎችን ሊተገብሩ ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም