የትግራይ ምክር ቤት የመንግስት ሰራተኞች አሰራር ረቂቅ አዋጅን ውድቅ አደረገ

60

መቀሌ መጋቢት 16/2011 የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ ምክር ቤት በመንግስት መስሪያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥ የተጠያቂነት ስርአትን ለመዘርጋት የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ ውድቅ አደረገ።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው በክልሉ ያለው የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የተለያዩ ችግሮች ያሉበት ነው በማለት ሳይቀበለው ቀርቷል።

ረቂቅ አዋጁ በህገ-መንግስቱ የተቀመጡ የዜጎች መብትና ሌሎች የስቪል ሰርቪስ አሰራሮችን የሚፃረር ሆኖ በማግኘቱ  ውድቅ አድርጎታል፡፡

አገልግሎት ሰጪው ከትራንስፖርት ጀምሮ ያልተሟሉለት በርካታ ችግሮች እያሉ ሰአት አሳልፎ በመምጣቱና  ከስራ ቀድሞ በመውጣቱ ሳይቀር በቀጥታ ከስራ እንዲባረር የሚለው ረቂቅ አዋጁ በክልሉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው ብሎታል።

አዋጁ ሲወጣ የመንግስት ፍላጎትን ጨምሮ የአገልግሎት ሰጪው መብትና ግዴታዎች ሚዛናዊ በሆነ መልክ ማቅረብ እንደነበረበት በምክር ቤቱ የህግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ታፈረ አስረድተዋል፡፡

"ረቂቅ ህጉ ሰራተኛውን ጨምሮ ህዝቡን በስፋት በማወያየት ሊዳብር ይገባዋል" ብለዋል።

አቶ ብርሃነ ተኹሉ የተባሉት  የምክር ቤቱ አባል "በአንድ አለቃ ከስራው እንዲሰናበት የሚያደርገው ረቂቅ አዋጅ ባለፈው ጥቅምት ምክር ቤቱ ያፀደቀውን የስቪል ሰርቪስ አሰራር የሚመለከት አዋጅ ላይ በዲስፕሊን ጉዳይ የተቀመጡ የደረጃ ሂደቶችን የሚፃረር ነው" ብለውታል።

የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሰብለ ካሕሳይ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው በሰጡት ማብራሪያ ረቂቅ አዋጁ ታሳቢ ያደረገው ተገልጋይ እያለ የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱና በመንግስት የስራ ሰአት የማይገኙ ሰራተኞች እንዲስተካከሉ ለማድረግ ነበር።

በዚህም በአገልግሎት አሰጣጡ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስተካከል ያግዛል ተብሎ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ተገልጋየ ህብረተሰብ የሚያነሳውን ቅሬታ ለማቃለል ያስችላል ተብሎ ታምኖበት የተዘጋጀ እንደነበረ አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ ከመቅጣት ይልቅ በአስተሳሰብ መቅረፅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ያሉት የምክር ቤቱ አባላት አዋጁ በቀጣይ ተሻሽሎና ጎልብቶ ይቅረብ በሚል በሙሉ ድምፅ ውድቅ አድርገውታል።

ከተለያዩ የውስጥ ገቢዎች የተገኘው ከ223 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በላይ ለካፒታልና ለመደበኛ በጀት እንዲውል የቀረበለትን የተጨማሪ በጀት አዋጅ ምክር ቤቱ አጽቋል።

ምክር ቤቱ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቅራቢነት ለክልሉ ምክር ቤት የቀረቡ 37 የወረዳና አንድ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ሹመት በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ የሁለት ቀናት ጉባኤውን ማምሻውን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም