ለውጡን ለማስቀጠል ከኦዴፓ ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ በነቀምቴ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ገለጹ

54

ነቀምቴ መጋቢት 16/2011 በክልሉና በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ  ቀጣይነት እንዲኖረው ከኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ በነቀምቴ ከተማ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ገለጹ፡፡

29ኛው የኦዴፓ  ምስረታ በዓል ዛሬ በነቀምቴ ከተማ  ሁለገብ አዳራሽ በውይይት ተከብሯል፡፡

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል የድርጅቱ አባል የሆኑት ዶክተር ተመስገን ጋሮማ በሰጡት አስተያየት ፓርቲው  ያስገኘው የፖለቲካና የልማት  ድሎች ቀጣይነት እንዲኖረው የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

" ይህ እውን እንዲሆን ሰላም ቀዳሚውን ስፍራ ስለሚይዝ  ፓርቲው በክልሉ ሰላምን ለማስፈን እያደረገ ያለው ጥረት በሁሉም ወገን ሊታገዝ ይገባል" ብለዋል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሳድያ አህመድ በበኩላቸው ከተሃድሶ ወዲህ የተገኘው ለውጥ የሴቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በአደባባይ  ያረጋገጠ በመሆኑ ለውጡን ለማሰቀጠል ከፓርቲው ጎን ተሰልፈው  የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በነቀምቴ ከተማና አካባቢዋ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦላቸው ያልተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲበቁ የክልሉን መንግስት የሚመራው ኦዴፓትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በሁሉም መስክ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ ቄሮዎች፣ አባገዳዎችና ምሁራን አስተባብረው ከፓርቲው ጋር  እንደሚሰሩ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል።

በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር የኦዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማቲዎስ ሶቦቃ በበኩላቸው   ፓርቲው ለህዝብ እራስ ምታት የሆነውን  የኪራይ ሰብሳቢነትና ፀረ-ዴሞክራሲ ተግባራትን  ለመግታት የጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

" በዓሉን ስናከብር መልካም ድሎችን እየጠበቅን፣ ሰላምና ልማት የማይፈልጉ ኃይሎችን በመለየት ለሕግ የማቅረብ ስራችንን በመስራት ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር  የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ቦጋለ ሹማ እንዳሉት የኦሮሞ ሕዝብ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ መሰረት የጣለ መሆኑን ገልጸው ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር ፓርቲ ይተጋል።

የከተማዋ ህዝብ ለእድገትና ብልጽግና ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በፍቅርና በመቻቻል በህብረት  እንዲሰራም አሳስበዋል።

የአካባቢውን ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴን ለመግታት የአባላቱና የደጋፊው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም