የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኟ ሕይወት በኤሌክትሪክ አደጋ አለፈ

66
ጊምቢ ግንቦት 24/2010 በምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ከተማ የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኟ ሕይወት በኤሌክትሪክ አደጋ አለፈ። በከተማው በሚገኘው መነ ሲቡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን ስትወስድ የነበረችው ተማሪ ማርታ ኤቢሳ ሕይወቷ በኤሌክትሪክ አደጋ ያለፈው ትናንት ከሰዓት በኋላ ነው። ከመንዲ ከተማ ራቅ ብሎ ከሚገኘው ቀራሮ ጉታ የገጠር ቀበሌ በመመላለስ ትምህርቷን ስትከታተል የቆየችው ወጣቷ ትናንት ከቀኑ 8፡00 አካባቢ አደጋው የደረሰባት የባዮሎጂና ሲቪክስ ፈተናን ለመውሰድ ወደትምህርት ቤቱ በመጣችበት ወቅት ነው። የመነ ሲቡ ወረዳ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጋሮማ ለኢዜአ እንደተናገሩት በሰዓቱ በጣለው ዝናብ ተማሪዋ በግቢው ውስጥ አዳልጧት ስትወድቅ የኤሌክትሪክ ገመድ ላይ በማረፏ ለአደጋው ተጋልጣለች። በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ አናት ላይ አልፎ የሚሄድ የኤሌክትሪክ ገመድ ተቆርጦ መሬት ላይ መውደቁ ለተማሪዋ ሞት ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል። ተማሪዋም በተቆረጠው የኤሌክትሪክ ገመድ ላይ ወድቃ መነሳት ሲያቅታት ተማሪዎች ተሯሩጠው ለመርዳት ቢጥሩም አለመቻላቸውን ገልጸዋል። በአካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይሉን በማቋረጥና ተማሪዋን ከያዛት የኤሌክትሪክ ገመድ በማላቀቅ ወደ መንዲ ሆስፒታል ተወስዳ የሕከምና እርዳታ ቢደረግላትም ሕይወቷን ማዳን አለመቻሉን ተናግረዋል። "የወደቀው የኤሌክትሪክ ገመድ እንዲነሳ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ለከተማው ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአምስት ቀን በፊት በተደጋጋሚ በስልክ ቢያሳውቅም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም" ብለዋል አቶ አለማየሁ። እንደ እርሳቸው ገለጻ በትምህርት ተቋማት እንዲህ አይነት መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ በትምህርት ቤቶች በኩል ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ትምህርት ቤቶች ከአደጋ የጸዱ መሆናቸውን በየጊዜው መፈተሽ እንደሚገባ ጠቁመው፣ የተማሪ ወላጆችም ሆኑ ማህበረሰቡ ልጆቻቸው ከተለያዩ አደጋዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ መምከር እንዳለባቸው አሳስበዋል። የመንዲ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክሌ ገብረሚካኤል በበኩላቸው ስለጉዳዩ በስልክ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በትምህርት ቤቱ አስተዳደር በኩል “የጀነሬተርና የኤልክትሪክ ኃይል አልተመጣጠነልንም” የሚል ጥያቄ በስልክ ከማሳወቃቸው ውጪ የኤሌክትሪክ ገመድ በትምህርት ቤቱ ግቢ ስለመውደቁ እምደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ46 ሺህ በላይ ተማሪዎች ዛሬ ከሰዓት በኋላ የሚጠናቀቀውን የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ከዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም