የትግራይ መልሶ መቋቋም ተቋም ተጠሪነት ለክልሉ ምክር ቤት ሆነ

91

መቀሌ መጋቢት 16/2011 የትግራይ ክልል ምክር ቤት የትግራይ መልሶ መቋቋም ተቋም/ትእምት/ ተጠሪነቱ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲሆን የቀረበለትን ሀሳብ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ፡፡

ምክር ቤቱ 5ኛ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባኤ ከትላንት ጀምሮ በሶስት የክልሉ ቢሮዎች ስራ አፈጻጸምና በቀረቡለት ረቂቅ አዋጆች ውይይቱን ቀጥሏል።

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሊያ ካሳ እንደገለጹት ትእምት ተጠሪነቱ ለክልሉ መንግስት እንዲሆን የተቋሙ የቦርድ አመራር ለክልሉ ምክር ቤት ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

ምክር ቤቱ በቀረበለት ሀሳብ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ሀሳቡን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

ትእምት የትግራይ ህዝብ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመቀረፍ ህዝቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ተጠሪነቱ ለክልሉ መንግስት መሆኑ የተሻለ ያደርገዋል ተብሎ እንደታመነበትም ተናግረዋል።

"የተቋሙ አመታዊ እቅድና አፈጻጸም የሚቀርበውም ለክልሉ መንግስትና ምክር ቤት ይሆናል" ብለዋል፡፡

ትእምት በምክር ቤት አባልነት ካቀፋቸው አካላት በተጨማሪም የሁሉም ወረዳ አፈ-ጉባኤዎች፣የህዝባዊ ማህበራት ሀላፊዎችን እንዲያካትት የቀረበለትን ሀሳብም ምክር ቤቱ አጽድቋል፡፡

ምክር ቤቱ ውይይቱን የቀጠለ ሲሆን ሁለት አዋጆችን አጽድቆ ማምሻውን ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ትእምት መሰቦ ሲምንቶ፣መስፍን ኢንዱስቱሪያል ኢንጂነሪንግ፣አልመዳ ጨርቃ ጨርቅና ሸባ ሌዘር ፋብሪካዎችና ሌሎችንም እንደሚያስተዳደር ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም