ከጎርፍ ጋር ተያይዞ ሊበከል በሚችል ውሃ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት---ጤና ጥበቃ ቢሮ

104
ባህር ዳር ግንቦት 24/2010 ከክረምት የዝናብ ጎርፍ ጋር ተያይዞ ሊበከል በሚችል ውሃ  ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ አሳሰበ። በቢሮው  የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች  መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር አቶ ተክለኃይማኖት ገብረህይወት ለኢዜአ እንደገለጸት የክረምት ዝናብ በሚያመጣው ጎርፍ ምክንያት የመጠጥና የምግብ ማብሰያ ውሃ በተለያዩ ባክቴሪያዎች የመበከል እድላቸው ከፍተኛ ነው። ውሃ ወለድ በሽታዎች ወደ ሰውነት የሚገቡበት ብቸኛ አማራጭ በአፍ ብቻ መሆኑን ጠቁመው " በሽታ አምጪ ባክቴሪያን ለመከላከል ዓይነተኛው አማራጭ ውሃን አፍልቶና አቀዝቅዞ መጠቀም ነው" ብለዋል። በክልሉ ከጤና ጣቢያ እስከ ሆስፒታል ድረስ የውሃ ማከሚያ ኬሚካሎች ስለሚገኙ  ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ወደ ሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ መጠቀም እንደሚችልና በበሽታው የተጠቃ ካለም መታከም እንደሚችል ጠቅሰዋል። ችግሩን ለመከላከል ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በጤና ባለሙያዎች አማካኝነት ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም ተመልክቷል። አቶ ተክለኃይማኖት እንዳሉት ባለፈው ዓመት በክረምት ወቅት በውሃ ብክለት ምክንያት ተከሰቶ በነበረው የአተተ በሽታ በክልሉ አራት ሺህ 791 ሰዎች ተጠቅተው ነበር። ህብረተሰቡ የውሃ ማከሚያ መድኃኒት መጠቀም የውሃውን ጣዕም ይቀይራል በሚል የጥንቃቄ ጉድለት በሽታውን ለመከላከል አስቸጋሪ እንደነበር ጠቅሰው ሆኖም   የውሃ ማከሚያ መድኃኒቱ በሳይንሳዊ መንገድ የተረጋገጠና በውሃው ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ እንደሌለው አመልክተዋል፡፡ በአማራጭነትም ህብረተሰቡ በቀላሉ ማድረግ የሚቻለውን ውሃን አፍልቶና አቀዝቅዞ መጠቀም ይኖርበታል። በሌላ በኩል ደግሞ  የወባ በሽታን ለመከላከል የሦስት ዓመቱ የአጎበር እደላ እንደሚደረግ ገልጸው ዘንድሮም አጎበር ከታደላቸው ሦስት ዓመት ለሞላቸው  ሦስት ሚሊዮን 400ሺህ ሰዎች ለማዳረስ እየተሰራጨ ነው ተብሏል፡፡ በሽታውን ለመከላከል ህብረተሰቡ በየአካባቢው ያለውን የኩሬ ውሃ ማፋሰስና የውሃ ንጽህናን መጠበቅ እንዳለበትም ተጠቁሟል። የባሀር ዳር ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሀዋ ሞሀመድ በሰጡት አስተያየት የጤና ባለሙያዎች በሚሰጧቸው ምከረ ሃሳብ መሰረት ውሃን አፍልቶ ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከወባ በሽታ እራሳቸውን ለመከላከልም አጎበርን በአግባቡ ከመጠቀም በተጨማሪ በደጃቸው የሚያቁሩ ቦታዎችን በማፋሰስ ላይ ናቸው። ውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል በቀላሉ አማራጭ የሆነውን ውሃን አፍልቶ መጠቀም እንደሆነ ተረድቶ ተግባራዊ እንደሚያደርግ የተናገረው ደግሞ ወጣት ጋሻው ወንዴ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም