የተጀመረው ለውጥ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን እንደሚሰራ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሜቴ አስታወቀ

68

ባህርዳር  መጋቢት 16/2011 በክልሉ ብሎም በሀገር ደረጃ  የተጀመረው ለውጥ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን እንደሚሰራ የአማራ ዴሞክራሲ ፓርቲ /አዴፓ/ ማዕከላዊ ኮሜቴ አስታወቀ፡፡

ማዕካላዊ ኮሚቴው በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሁለት ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን ግምገማ አጠናቋል፡፡

ግምገማውን አስመልክተው የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ዮሐንስ ቧያለው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ለውጡን ዳር የሚያደርሱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡

ከለውጡ ጋር በተያያዘ የሰዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚረጋገጡበት ሁኔታ እየተመቻቸ መምጣቱንና መሻሻሎች መታየታቸውን ማዕካላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

ከለውጥ ፈላጊውና ከለውጥ መካች ኃይሎች ጋር በተፈጠረው ችግርም አለመረጋጋትና የዜጎች መፈናቀል ተባብሶ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህንን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል፡፡

የህግ የበላይነትን የሚሸረሽሩ አካሄዶች በስፋት እንደነበሩ ገልፀው አሁን ላይ አንፃራዊ መሻሻል ማሳየቱንም ገልጸዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ እንዳሉት  የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ብሎም የክልሉን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በአስተማማኝ ለውጥ ለማድረስም በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ሆኖም በትግል የመጣውን ነፃነት በመጠቀም አልፎ አልፎ የሰላም መድፍረስ፣ የህግ የበላይነት መጣስና  የፀጥታ ችግር ያልተፈቱ ጉዳዮች እንዳሉ ማዕከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

አዴፓ በለውጡ የተጋረጡ ችግሮችን ለመፍታት ብቻ ሳይሆን ፓርቲው እንዲጠናከርና የአማራን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር የሚያግዙ ተግባራትን ያከናውናል፡፡

" በክልሉ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ በማካሄድ ብጥብጥ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የለውም"  ያሉት አቶ ዮሐንስ ይህንን ለማስተካከልም መንግስትና ህዝቡ በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ህዝበ ከሌሎችም ኢትዮጵያዊያን ጋር ለዘመናት የዘለቀው ወንድማማችነቱ የበለጠ ጠንክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ለውጡ እንዲመጣ የሰሩት የኦዴፒ እና የአዴፓ ድርጅታዊ ግንኙነትም ጠንካራና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የለውጡ ፍጥነት እንዲጨምር ተጋግዘው እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የክልሉን መንግስት የሚመራው አዴፓ ሰላም ፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና  የልማት መሪ ሆኖ ከመተግበር ባለፈ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራና የቀጣይ የመኸር እርሻ እንቅስቃሴም በተለየ ተልዕኮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡

"ወጣቱ፣ ምሁራን፣ ባለሃብቱ፣ በውጭ የሚኖሩ የአካባቢ ተወላጆችና መላ ህብረተሰቡ ፓርቲው ጠንካራ ሆኖ እንዲወጣና የህዝቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ ከልብ እየደገፉ ይገኛሉ "ብለዋል፡፡

ይህን መነሳሳት በመጠቀምም አዴፓና የክልሉ መንግስት በሁሉም መስክ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖርና ለውጡ የተሻለ ውጤታማ እንዲሆን እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

የለውጡ ደጋፊ አካላትም የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር እንዲደርስ እንደ እስከ አሁን ቀደሙ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ፓርቲውን የበለጠ ለማጠናከር ያግዛሉ ያላቸውን ዶክተር አምባቸው መኮንንን የአዴፓ  ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡

እንዲሁም አቶ ዮሐንስ ቧያለውን እና አቶ ላቀ አያሌውን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አድረጎ መምረጡ ታውቋል፡፡

አዴፓ በባህር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው ግምገማም የውደፊት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ አጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም