ወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ ካይሮ በሚካሄደው የአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድር ይሳተፋሉ

147

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2011 በግብጽ በሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።

በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን (CAV) አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ውድድር ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዚያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ካይሮ በሚገኘው የአልሀሊ ቮሊቦል ጅምናዚየም ይካሄዳል።

በውድድሩ 24 የአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ሁለቱ ክለቦች በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት በአፍሪካ መረብ ኳስ ኮንፌዴሬሽን አማካኝነት ለኢትዮጵያ ክለቦች በተደረገ ግብዣ ነው።

ወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት በ2010 ዓ.ም  የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ በመውጣታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ሁለቱ ክለቦች ለውድድሩ ዝግጅት ይረዳቸው ዘንድ ከዛሬ ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ልምምድ እንደሚጀምሩም ጠቅሰዋል።

ወላይታ ድቻ በ2007 እና በ2010 ዓ.ም በተካሄደው የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ተሳትፎ ማድረጉንና በሁለቱም አጋጣሚ ከምድቡ ማለፍ ሳይችል መቅረቱን አስታውሰዋል።

በአፍሪካ ቮሊቦል የክለቦች ውድድር ኢትዮጵያዊያን ክለቦች መሳተፋቸው ልምድ እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር ከአፍሪካ ክለቦች አንጻር ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በግብጽ ካይሮ በተካሄደው 37ኛው የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር የአገሪቷ ክለብ አል ሀሊ አሸናፊ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የአፍሪካ ቮሊቦል ኳስ ክለቦች ውድድር እ.አ.አ በ1987 የተጀመረ ሲሆን የግብጹ አልሀሊ 13 ጊዜ፣ የቱኒዚያው ሲኤስ ሰፋክሲያን ስድስት እንዲሁም የግብጹ ዛማሌክ አምስት ጊዜ አሸናፊ ሆነውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም