የምእራብ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም ማሳቸውን በዘር እየሸፈኑ ነው

67
አምቦ ግንቦት 24/2010  በምእራብ ሸዋ ዞን  የሚገኙ አርሶ አደሮች በአከባቢያቸው እየጣለ  ያለውን ዝናብ በመጠቀም  ማሳቸውን  በዘር በመሸፈን ላይ መሆናቸውን ገለፁ፡፡ በዞኑ በዘንድሮው የመኸር ወቅት 615 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለማልማት የሚያስችል የእርሻ ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡ የኢሉ ገላን ወረዳ የቶሊ ቀበሌ አርሶ አደር ቶለሳ ፊጣ በሰጡት አስተያየት ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በአካባቢያቸው እየጣለ ያለው ዝናብ ለእርሻና ለዘር ስራ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ ይህንኑ ምቹ ሁኔታ በመጠቀምም አንድ ሄክታር ማሳቸውን በበቆሎና ኑግ ዘር ሸፍነው በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ሌላው የሊበን ጃዊ ወረዳ የጮቢ ቀበሌ አርሶ አደር ሙለታ ቱፋ በበኩላቸው እስካሁን ያለው የዝናብ  ስርጭት የተስተካከለና ለእርሻ ስራ ምቹ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዝናቡን በመጠቀምም እስካሁን ግማሽ ሄክታር ማሳ በማሽላ ዘር የሸፈኑ ሲሆን 1 ነጥብ 5 ሄክታር ማሳቸውን ደግሞ በጤፍ ዘር ለመሸፈን የእርሻ ስራ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የምእራብ ሸዋ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የአዝእርት ልማት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ድሪሪሳ በበኩላቸው በ2010/011 ምርት ዘመን 615 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለማልማት የሚያስችል የእርሻ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እስካሁን በተደጋጋሚ ታርሶና ለስልሶ ለዘር ከተዘጋጀው 500 ሺህ ሄክታር መሬት ውሰጥ 53 ሺህ 645 ሄክታር የሚሆነው ቀድሞ በሚዘራው በቆሎና ማሽላ ዘር ተሸፍኗል፡፡ የዘር ስራው እስከ ነሐሴ አጋማሽ 2010 ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው ለልማቱ የሚሆን የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአርሶ አደሩ ጉልበት የተዘጋጀ  ግማሽ ሚሊዮን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያም  ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። በመኸር ወቅት ከሚለማው 615 ሺህ ሄክታር መሬት 19 ነጥብ 3  ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመስብሰብ መታቀዱን አቶ ተስፋዬ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በዞኑ ባለፈው መኸር ከለማው መሬት  17 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል መሰብሰቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም