በኦሮሚያ 6ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል ዘር ለመሸፈን ዝግጅት እየተደረገ ነው

57

ነቀምት መጋቢት 16/2011 በኦሮሚያ ክልል በ2011/12 የምርት ዘመን 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ለመሸፈን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን  የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ደሣለኝ ዱጉማ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት በምርት ዘመኑ ለበልግና መኽር ወቅቶች የሚሆን የማዳበሪያና ምርጥ ዘር እየቀረበ ነው ።

የግብርና ባለሙያዎችም አርሶ አደሩን በሙሉ አቅማቸው እንዲያገለግሉና በቅርበት ድጋፍ እንዲሰጡ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከምስራቅና ምዕራብ እንዲሁም ከቄለምና ሆሮጉድሩ ወለጋ ዞኖች ለተውጣጡ 708 የግብርና ባለሙያዎች ባለፈው ሳምንት ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም  የግብርና ባለሙያዎች  አርሶ አደሩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በአግባቡ በመጠቀም ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የአካባቢያቸውን  ሠላም የማረጋገጥ ኃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም