ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር አንድነቱን ጠብቆ ለውጡን ማስቀጠል ይጠበቅበታል---ኡዝታዝ አቡበክር አህመድ

65

ደሴ መጋቢት 16/2011 " ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ተረዳድቶና ተደጋግፎ አንድነቱን በመጠበቅ ለውጡን ማስቀጠል ይጠበቅበታል"  ሲሉ የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡዝታዝ አቡበክር አህመድ ገለጹ፡፡

የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በደቡብ ወሎ ሐይቅ ከተማ ህዝባዊ ውይይት አካሄዷል፡፡

የኮምቴ ሰብሳቢ ኡዝታዝ አቡበክር እንደገለጹት ለሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም በየእምነቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የተጀመረው የሀሳብና የእምነት ነጻነት እንዳይቀለበስ ከሌሎች የእምነት ተከታይ ወድሞቻችን ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎች የኢትዮጵያን የጥንት አንድነት፣መቻቻልና የአብሮነት ባህልን  ለትውልዱ  በማስተማር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

" ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ተረዳድቶና ተደጋግፎ አንድነቱን በመጠበቅ ለውጡን ማስቀጠል ይጠበቅበታል " ያሉት ኡዝታዝ አቡበክር ወጣቱም ከአባቶቹ ታሪክን በመማር ተቻችለው ሰላሙን ነቅቶ እንዲጠብቅ መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡

ግፍ በግፍ እንደማይመለስ ተናግረው  የትላንቱን ጭቆና አስታውሶ ነገን ማጨለም የዋህነት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

የትኛውንም እምነትና ብሄር የማይወክሉ እያስመሰሉ ለመከፋፈልና እርስ በእርስ ለማጫረስ የሚሞክሩ ግለሰቦችን በመምከርና ለህግ አጋልጦ መስጠት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በውይይቱ መድረኩ የተገኙት ሼህ ሐሚድ ሙሳ በበኩላቸው "በየእምነት ተቋሙ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምንና መቻቻልን በመስበክ ሀገራዊ ለውጡን በማስቀጠል ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡

ከመበዳደል፣ ከመበሻሻቅና ከመጠላላት በመቆጠብ  አንድ በሚያደርጉ  ጉዳዮች ላይ በማተኮር በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ እንዲሰፍን ማድረግ የሁሉም ድርሻ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ወጣቱ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ምክንያታዊና አርቆ አሳቢ  መሆን እንዳለበትም ያመለከቱት ደግሞ ሌላው የመድረኩ ተሳተፊ ሼህ ሙሃመድ ሐሚዲን ናቸው፡፡

" የበላይና የበታች ሳንል ለመከበር ሌላውን ማክበር ይቀድማል" ብለዋል፡፡

የክርስትና እምነት ተወካይ ሊቀ ሰይማን ታደሰ ኃይሌ በበኩላቸው " በየደረጃው  በሚፈጠሩ መደረኮችና በየእምነት ተቋሙ መጽሃፍ ቅዱስና ቅዱስ  ቁርዓንን ለትውልዱ በማስተማር አንድነታችንና ሰላማችንን እንጠብቃለን " ብለዋል፡፡

የመቻቻልና የአብሮነት ባህልን   በማጠናከር በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ለመከፋፈልና ለውጡን ለመቀልበስ በሚሞክሩ ግለሰቦች መታለል እንደማይገባም መክረዋል፡፡

የሐይቅ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ  አቶ ከበደ ካሳ ከኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር በመወያየት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማንኛውንም እምነትና ተግባር ያለ ሰላም መከወን ስለማይቻል ከሁሉም በፊት ሁሉም የአካባቢውን ሰላም ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቆራኝቶ እንዲጠብቅም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመድረኩ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ኡለሞችና  ኡዝታዞች ተገኝተዋል፡፡

ለአማራ ክልል ተፈናቃዮች ድጋፍ የሚውል ከ130 ሺህ ብር በላይ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መሰብሰብ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም