በፓርኩ የተነሳው ሰደድ እሳት የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

100

ጎባ መጋቢት 16/2011 በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ክልል ውስጥ የተነሳውን የሰደድ እሳት የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በሕብረተሰቡና በፀጥታ አካላት ተሳትፎ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተመለከተ፡፡

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስቻለው ጋሻው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት የሰደድ እሳቱ ከትናንት ጀምሮ የተከሰተው በዞኑ ጎባና ዲንሾ ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡

እሳቱ የተነሳበት የፓርኩ ክልል በቀላሉና በፍጥነት በሚቀጣጠሉ የእስት ዛፎች ዝርያ መሸፈኑ እሳቱ ፈጥኖ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት የሰደድ እሳቱን ለመቆጣጠር ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ እሳቱን እንዲነሳ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የአካባቢው ፖሊስ በህግ ቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ መሆኑንም አብራርቷል፡፡

" ማህበረሰቡ ከፓርኩ በኢኮ-ቱሪዝምና ተያያዥ ጉዳዮች የሚገኘውን ጥቅም እንዲጋራና ባለቤትነቱን እንዲያጎለብት በማድረግ እየደረሰበት ያለውን ጫና ለመቀነስ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አቶ አስቻለው ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 

በእሳት ማጥፋት ሂደት ላይ ከተሳተፉ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሙአዝ ኤሊያስ እንደተናገሩት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከአገር አልፎ የዓለም ቅርስ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው።

በአሁኑ ወቅት በደኑ ላይ ተደጋጋሚ የእሳት አደጋ መከሰቱን አስታውሰው የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትና የሕብረተሰብ ክፍሎች ለችግሩ ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

" በደኑ ላይ በየጊዜው እሳት ሲነሳ ተከታትሎ ከማጥፋት በተጨማሪ በህገ ወጦች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ሊጠናከር ይገባል" ያሉት ደግሞ አቶ ማህሙድ ተማም ናቸው ።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በጊዜያዊ መዝገብ ላይ የተመዘገበና የተለያዩ ብርቅዬ የዱር አራዊትና አእዋፍ መገኛ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም