በሶማሌና በኦሮሚያ ከ5ሺህ 900 ለሚበልጡ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ መሬት ተሰጠ

66
ጅግጅጋ/አምቦ  ግንቦት 24/2010 በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከ5ሺህ 900 ለሚበልጡ መምህራንና ሌሎች ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ መሬት የተሰጣቸው መሆኑ ተገለጸ፡፡ የቤት መስሪያ መሬት ከተሰጣቸው መካከል በሶማሌ ክልል ከ5ሺህ በላይ መምህራን ቀሪ ደግሞ በኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ ዞን ለሚገኙ ነዋሪዎች ነው፡፡ የሶማሌ ክልል መምህራን ማህበር ሊቀመንበር አቶ ከደር ዩሱፍ እንዳሉት ለመምህራኑ የተሰጠው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለእያንዳንዳቸው 250 ካሬ ሜትር ከባለቤትነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ጋር ነው፡፡ "በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ተመድቦ በመስራት ላይ ከሚገኙ 25 ሺህ መምህራን ውስጥ ባለፉት ሶስት ወራት በመጀመሪያ ዙር አምስት ሺህ ስምንት መቶ ሃምሳ ስምንት ያህሉ የእድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል" ብለዋል፡፡ መምህራኑ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ በነፃ ማገኘታቸው በስራቸው ላይ ተረጋግተው በስራቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛል፡፡ መምህራኑ በሚሰሩበት ከተማ ላይ መሬት እንዲያገኙ መደረጉ ለቤት ኪራይ የሚያወጡት የነበረውን ወጪ እንደሚያስቀርላቸው ተናገሩት የቀብሪበያህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር አቶ አብዲሰላም በሽር ናቸው፡፡ ለተሰጣቸው መሬት አመስግነው በመሬቱ ላይ ቤት ለመገንባት አቅም ያለው መምህር አነስተኛ በመሆኑ መንግስት የገንዘብ ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ በሚያመቻችላቸው አንደሚፈልም ጠቁመዋል፡፡ የቀብሪበያህ ከተማ አስተዳደር ከንቲባው  አቶ ሙክታር መሀሙድ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር በስራቸው ላይ የሚኖረው ተፅእኖ በመረዳት ለ300 መምህራን መንገድ ፣መብራት እና የውሃ መሰረተ ልማት በተዘረጋበት አከባቢ መሰጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሀሙድ አህመድ እንደገለጹት  መንግስት የመምህራን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል በወሰደው እርምጃ ብዛት ያላቸው መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ  ቦታ ባለቤት ሆኗል፡፡ መምህራኑ የቤት መስሪያ ገንዘብ ከሶማሌ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻችላው መሆኑንም ጠቅሰዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጄሬ ወረዳ በማህበር ለተደራጁ 918 ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተስጥቷል፡፡ ካለፈው ሳምንት ወዲህ የቤት መስሪያ ቦታው የተሰጠው በ40 ማህበራት ለተደራጁ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆኑን የወረዳው የከተማ መሬትና ልማት ማኔጅመንት ጸህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተፈሪ ዘለቀ  ተናግረዋል፡፡ ለማህበራቱ አባላት በነፍስ ወክፍ 200 ካሬ ሜትር ቦታ የደረሳቸው ሲሆን ከመካከላቸውም የመንግስት ሰራተኞች፣ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ይገኙበታል። በቀጣይም የወረዳውን ነዋሪ የከተማ ቦታ ጥያቄ ፍላጎት ለማሟላት የቦታ ዝግጅት እየተደረገ  መሆኑንም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ በወረዳው የኤጄሬ ከተማ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ፊዳ በሰጡት አስተያየት ለረጅም ጊዜ በግለሰብ ቤት ተከራይተው በመኖር ለተለያየ ችግር እንደነበረባቸው ጠቁመው አሁን በተሰጣቸው ቦታ የራሳቸውን ቤት በመስራት የተረጋጋ ሕይወት ለመምራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌላው የመንግስት ሰራተኛ  ወይዘሮ አሰለፍ ዘሪሁን በበኩላቸው ከአራት ልጆቻቸው ጋር በግለሰብ ቤት ተከራይተው እንደሚኖሩ ገልጸው በተለይ በየጊዜው የቤት ኪራይ ዋጋ እየጨመረ መቸገራቸውን ገልጸዋል። ወይዘሮ አሰለፍ እንዳሉት መንግስት የቤት ችግራቸውን ተረድቶ በሰጣቸው ቦታ በአጭር ጊዜ ቤት ገንብተው ለመግባት አቅደዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም