በትግራይ የብድር ገንዘብ አመላለስ ላይ የአመራሩ ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ

67

መቀሌ መጋቢት 16/2011 በብድር የወጣ የመንግስት ገንዘብን በማስመለስ ረገድ የአመራሩ ጥረት ዝቅተኛ መሆኑን የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

በክልሉ ለግብርና ግብአት መግዣ ከተወሰደው ብድር እስከ አሁን ከአንድ ቢልዮን ብር በላይ እንዳልተመለሰ ተመልክቷል።

ትላንት ከሰዓት በኋላ ጉባኤውን የጀመረው የምክር ቤቱ አምስተኛ ዘመን አስራ አምስተኛ መደበኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች እንደገለጹት በየደረጃው የሚገኘው የክልሉ አመራር የብድር ገንዘብን የማስመለስ ተሳትፎው አነስተኛ ነው።

የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገበ በብድር አመላለሱ ዙሪያ የተከናወኑ ስራዎችን ሪፖርት አቅርበዋል።

"በክልሉ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች ካለው አንድ ነጥብ አንድ ቢልዮን ከሚሆነው ገንዘብ ባለፉት ወራት ለማስመለስ በተደረገው ጥረት 35 ሚልዮን ብር ብቻ ተሰብስቧል" ብለዋል።

ብድር ለማስመለስ እየተደረገ ባለው ጥረትም በየደረጃው ያለው የክልሉ አመራር የሚያደርገው ተሳትፎ የተፈለገውን ያህል አለመሆኑን ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም "በብድር አመላለስ አመራሩ እራሱ ሞዴል እንዲሆን ማድረግ የሚያስፈልግ በመሆኑ በቀጣዮቹ ወራት በትኩረት ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።

በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አብርሃ በበኩላቸው ከ117 ሺህ የሚበልጡ በተለይ በታችኛው እርከን ያሉ አመራሮች ከ168 ሚልዮን ብር በላይ እንዳልመለሱ አስረድተዋል።

በክልሉ ያሉት ህብረት ስራ ማህበራት የወሰዱትን ብድር በወቅቱ ባለመክፈላቸው በቅርቡ 104 ሚልዮን ብር በቅጣት መልክ እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ምሕረት በርሀ አመራሩ ራሱ ምሳሌ ካልሆነ ሌላውን እንዲከፍል ማድረግ እንደማይችልም ተናግረዋል።

የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ዕፃይ እምባዬ በበኩላቸው ገንዘቡ ሳይሰበሰብ ለበርካታ አመታት በመቆየቱ በክልሉ በጀት ላይ ተፅእኖ እያስከተለ መሆኑንም አስረድተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ላይ ከተወያዩ በኋላ መንግስት ወደ ሌላ እርምጃ ከመግባቱ በፊት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አመራሩ ለማስመለስ መስራት እንዳለበት ወስነዋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው እለትም በሌሎች ጉዳዮች ላይ በመወያየት ተጨማሪ በጀት ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም