የህዳሴ ግድብ የመሠረተ ድንጋይ የተጣለበትን ስምንተኛ ዓመት በመቀሌ በፓናል ውይይት ተከበረ

416

መቀሌ መጋቢት 15/2011 የትግራይ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ስምንተኛ ዓመት ዛሬ በመቀሌ  ከተማ በፓናል ውይይት አከበረ።

ከክልሉ ለግድብ ግንባታ ከተዘጋጀው ቦንድ 614 ሚሊዮን ብር ተሸጧል።

የግድቡ ፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸም የኢንጂነሪንግ ሳፖርት ኦፊስ ክፍል ኃላፊ ኢንጂነር ኤርሚያስ ውብሸት በፓናሉ ላይ የግድቡ የግንባታ አፈጻጸም የደረሰበትን ደረጃና የገጠሙትን ተግዳሮቶች አስረድተዋል።

ግድቡን በአምስት አመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም  የሲቪል ስራውን የወሰደው ሳሊኒ ኩባንያ በመሠረት ቁፋሮ ሂደት በገጠመ ጥልቅ ሸለቆ በኮንትራት ከተያዘለት ዕቅድ  ሦስት ዓመታት እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ከፕሮጀክቱ ግንባታ ከ66 በመቶ በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም የሲቪል ስራዎች 83 በመቶ  የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የአቃፊ ግድብ/የሳድል ዳም/ግንባታ 93 በመቶ መድረሱን  አስታውቀዋል።

ግድቡ ለመገንባት ከሚያስፈልገው 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ኮንኩሪት ሙሊት ተከናውኗል።

ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን(ሜቴክ)ተሰጥቶት የነበረው የኤሌክትሮና ኃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች ዝቅተኛ አፈጻጸም እንደነበራቸው አስታውሰዋል።

የትግራይ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ገብረ ሚካኤል መለስ ከትግራይ ክልል ሕዝብ በቦንድ ግዢ ብቻ እስከ ታኅሣሥ ወር 2011 ድረስ  614 ሚሊዮን መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በፓናል ውይይት ከተሳተፉት መካከል ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥረው በወር በሚያገኙት ገቢ የሚያስተዳድሩት አቶ ኪሮስ ማርታ አንዱ ናቸው።

በወር ከሚከፋፈላቸው 4 ሺህ ብር  ደሞዝ በየወሩ የ1ሺህ 500 ብር ቦንድ እንደሚገዙና በየካቲት ወር ደሞዛቸው  ለ82ኛ ጊዜ ቦንድ ገዝተዋል።

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ በየወሩ ቦንድ መግዛታቸውን እንደማያቋርጡ የገለጹት አቶ ኪሮስ፣ ግድቡን አስመልክቶ የሚወጡ የተምታቱ  መረጃዎች በድጋፍ ሰጪዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚያደርሱ ጥንቃቄ እንዲደረግ ተናግረዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ሲሳይ የሺሀረግ በበኩላቸው ለድጋፉ ቀጣይነት ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ትክክለኛ መረጃ መነገር እንዳለበት ጠቁመዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሕዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር የግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት በዓል አከባበር ኅብረተሰቡ በግድቡ ያለውን አመኔታ ለመመለስ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የትግራይ ክልልን ጨምሮ በአዲስ አበባና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል  መድረኮች መዘጋጀታቸው አስታውሰው፣በቀጣይም በሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ  መድረኮች እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡