ለተደጋጋሚ የእሳት አደጋ እየተጋለጠ ባለው የኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ተቋም ሊኖር ይገባል ተባለ

287

ሱሉልታ መጋቢት 15/2011በኦሮሚያ ክልል የፊንፊኔ ዙሪያ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ያሉበት አካባቢ በመሆኑ በአቅራቢያው የእሳትና ድንገተኛ ተቋም ሊኖር እንደሚገባ ተገለፀ።

ከአዲስ አበባ የእሳት አደጋ ስጋት ኮሚሽን በተገኘው መረጃ መሰረት በዚህ አካባቢ በተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ይከሰታል፤ ሆኖም የእሳት አደጋውን የመከላከል ተግባሩ የሚከናወነው ከመሃል አዲስ አበባ በሚመጡ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ባለሙያዎች ነው።

ሆኖም ከአዲሰ አበባ የሚንቀሳቀሰው የእሳት አደጋ መከላከል ቡድን ወደስፍራው አስኪደርስ ጊዜ የሚወሰድ በመሆኑ ብዙውን ጊዜ በአካባቢው በሚከሰቱት የእሳት አደጋዎች ከፍተኛ ንብረት ይወድማል።

በሱልታ ከተማ በአቢሲኒያ ሻማ ፋብሪካ ላይ ዛሬ የደረሰውን የእሳት አደጋ ለመዘገብ ወደስፍራው አቅንቶ የነበረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ያነሱትም ይህንኑ ነው።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በአካባቢው በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚከሰቱ የእሳት አደጋዎችን በፍጥነት በመከላከል የሰው ህይወትንና ንብረትን ማዳን እንዲቻል በአቅራቢያው የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ ተቋም ሊኖር ይገባል። 

ጉዳዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን በዛሬው አደጋ ቦታ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ የእሳት አደጋ ስጋት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር አህመድ መሃመድም ይስማማሉ።

እርሳቸው እንዳሉት በዞኑ ተደጋጋሚ አደጋዎች እየደረሰ በመሆኑ የእሳት አደጋ መከላከያ ተቋም ያስፈልጋል።

የሱሉልታ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ ሮዛ ዑመር በበኩላቸው በከተማ ብዙ ፋብሪካዎች ስላሉ የድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ ተቋም ማቋቋም ያስፈልጋል ብለዋል።

አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት አንድ የእሳት መከላከያ ተሽከርካሪ እየገዛ መሆኑን ጠቁመው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ባለሙያዎችን ለማሰልጠንና ለፋብሪካ ባለቤቶች የአደጋ መከላከል ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ኮማንደር አህመድም ለቅርብ ጊዜ መፈትሄ ይሆን ዘንድ ፋብሪካዎች የእሳት መከላከያ ሴፍቲ መጠቀም አለባቸው፣በረጅም ጊዜ ግን የእሳት አደጋ ተቋም መቋቋም ያስፈልጋል ብለዋል።

የፋብሪካው የአክሲዮን ባለድርሻ መንሱር ኑር በበኩላቸወ የእሳት አደጋው ተቋም በአካባቢው ቢኖር ፋብሪካቸው በከፊል የመትረፍ ዕድል ይኖረው ነበረ ይላሉ።

“እዚህ አከባቢ ላይ እሳት አደጋ ባለመኖሩ ትልቁ ችግር ነው።እሄን ነገር በቀላሉ መከላከል ይቻል ነበር።ገና ከአዲስ አበባ መጥቶ እስኪ ደርስ ድረስ  ችግር ተፈጥሯል።ቢያንስ እዚህ በጎን በኩል የነበረው ማሽኖቹ ናቸው፣በላይ በኩል ያለው ጥሬ ዕቃ ነው።በቅርብ ጊዜ የገባ ጥሬ እቃ ነበር። በቅርበት የእሳት አደጋ ሰራተኞች ቢኖሩ ኖሮቢያንስ  ማሽኑን ማትረፍ ባይቻል፣ጥሬ ዕቃውን ማትረፍ ይቻል ነበር” ብላል።

በሱሉልታ ከተማ ዛሬ ጠዋት በደረሰ እሳት ንብረትነቱ የዋጃጆ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሆነው አቢሲኒያ ሻማ ፋብሪካ ሙሉ ለሙሉ የተቃጠለ ሲሆን በፋብሪካው አጠገብ የሚገኘው አሳዬ ዘይት ፋብሪካ ደግሞ መጠነኛ ቃጠሎ ደርሶበታል።