ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገውን ድጋፍ በተቀናጀ መንገድ የሚመራ የማስተባባሪያ ማዕከል ሊቋቋም ነው

65

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2011 በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞንና አካባቢው ከፀጥታ ስጋት ጋር በተያያዘ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገውን ድጋፍ በተቀናጀ መንገድ ለመምራት የሚስችል የማስተባባሪያ ማዕከል ሊቋቋም ነው።

''የአስቸኳይ ጊዜ  ድጋፍና ምላሽ ማስተባበሪያ'' በሚል ስያሜ የሚጠራው ማእከሉ የሚቋቋመው በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ውስጥ ነው።

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ከ311 ሺህ የሚልቁ የጌዴኦ የተፈናቃዮች በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑ ተጠቁሟል። 

ከዚህም ሌላ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን  ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በራስ ተነሳሽነት ለእነዚህ ተጎጂዎች ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

እናም በመጪው ሳምንት ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ማእከሉ በተለያየ መንገድ እየተሰባሰበ ያለውን ይህንን ሰብአዊ ድጋፍ በተቀናጀ መንገድ ለመምራት የሚያስችል መሆኑን ብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ደግሞ አጠቃላይ ሥራውን በበላይነት ይመራል ነው የተባለው።

የኮሚሽኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ማዕከሉ የክልል፣ የዞንና ወረዳ አካላት፣ የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ይሳተፉበታል።

የማስተባበሪያ ማዕከሉ መቋቋም ከተለያዩ አካባቢዎች እየቀረበ ያለው ሰብአዊ ድጋፍ ስርዓት ባለው መንገድ እያሰባሰበ በአግባቡ ለተጎጂዎቹ እንዲደርስ ለማድረግ  ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ካለፈው ጥር ጀምሮ እስከ መጪው ሰኔ ወር መጨረሻ  ድረስ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች የተፈናቀሉ ሲሆን 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በድርቅ ሳቢያ ከቀያቸው የወጡ ቋሚ እርዳታ የሚፈልጉ ናቸው። 

በግጭት ከተፈናቀሉ ውስጥ  ከ208 ሺህ የሚልቁት በጌዲኦ የሚገኙ ሲሆን በመንግስትና በለጋሽ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።

በተያዘው መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ  በፀጥታ ስጋት ችግር ሌሎች ከምዕራብ ጉጂ  የተፈናቀሉ ከ103 ሺህ በላይ ዜጎች እነዚህን ተፈናቃዮች መቀላቀላቸውን  ከክልሉ የደረሰውን መረጃ የጠቀሰው ኮሚሽኑ አመልክቷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም