የኢትዮጵያ እጅ ኳስ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ መጋቢት 15/2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በተካሄዱ ተስተካካይ ጨዋታዎች ፍጻሜውን አግኝቷል።
በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም መከላከያ ድሬዳዋ ከተማን 30 ለ 22፣ ፌዴራል ፖሊስ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 30 ለ 27 አሸንፈዋል።
ዱራሜ ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከምባታ ዱራሜን 35 ለ 30 በማሸነፍ የሊጉን የመጀመሪያ ዙር ውድድር በመሪነት ማጠናቀቅ ችሏል።
በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ያደረጋቸውን ዘጠኝ ጨዋታዎች ሲያሸነፍ በአንጻሩ ጎንደር ከተማ ያደረጋቸውን ዘጠኝ ጨዋታዎች ተሸንፏል።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ18 ነጥብ ሲመራ፤ የአምናው የሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ15 ነጥብ፣ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ13 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ጎንደር ከተማ ያለ ምንም ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
10 ክለቦች እየተሳተፉበት የሚገኘው የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ውድድር ታህሳስ 27 ቀን 2011 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል።
የትናንት ጨዋታዎችን ተከትሎ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር የተጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ውድድር ከሚያዝያ አጋማሽ በኋላ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የ2011ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛው የውድድር ዓመቱ ነው።
ፕሪሚየር ሊጉ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን፤ መከላከያ በ2009 ዓ.ም እንዲሁም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ያለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።