ኢትዮጵያ ከገጠሟት ችግሮች ለመላቀቅ የሁሉም ዜጋና የፓርቲዎች የጋራ ርብርብ ወሳኝ ነው- ነእፓ

61

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2011 ኢትዮጵያ ከገጠማት ወቅታዊና የረዥም ጊዜ ችግሮች ለመላቀቅ የሁሉም ዜጋና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ርብርብ ወሳኝ እንደሆነ የነፃነትና የእኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ገለጸ።

የነፃነትና የእኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) አባለቱ ፣ ደጋፊዎቹና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ዛሬ የመመስረቻ ጉባዔውን በአዲስ አበባ አካሄደ።

የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አብዱልቃድር አደም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከገጠማት ወቅታዊና የረዥም ጊዜ ችግሮች  ለመላቀቅ የሁሉም ዜጋ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ርብርብ ወሳኝ ነው።

ለዚህም የነጻነትና የእኩልነት ፓርቲ አገሪቷ ካሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመላቀቅ በምታደርገው እንቅስቃሴና የሃገሪቷ መፃሂ እድል በጎ እንዲሆን እንዲሁም ሰላምና እድገት እንዲሰፍን የራሱን አስተዋጾኦ ለማበርከት የተቋቋመ ፓርቲ ነው ብለዋል።

በአገሪቷ ሰብዓዊና ዴሞክራሲ መብቶች እንዲከበሩ፣ የመልካም አስተዳደር መርሆዎች እንዲተገበሩ፣ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን እንዲሁም የፖለቲካ ስልጣን ከህዝብ የሚመነጭ የፖለቲካ ባህል እንዲሆን እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብታቸው እንዲከበርና የሚዲያና የሲቪክ ማህበራት በሀገር ግንባታ ውስጥ ሰፊ ሚና እንዲኖራቸው ፓርቲው እንደሚታገልም ጠቁመዋል።

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ከልዩነት ይልቅ አንድነት፣ ከመከፋፋል ይልቅ መሰብሰብ፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ከግጭት ይልቅ ሰላም፣ ከመወጋገዝ ይልቅ መተጋገዝን፣ ከጥርጣሬ ይልቅ መተማመን እንዲሰፍንና እውነተኛና አስተማማኝ እህትማማችነትና ወንድማማችነት እንዲነግስ ይሰራል ሲሉም አመልክተዋል።

የፓርቲው መስራች ጉባዔ ዝግጅት ኮሚቴ አቶ አብዱረህማን ተካ በበኩላቸው የነፃነትና የእኩልነት ፓርቲ  የምርጫ ቦርድን ሀገራዊ ፓርቲን ለሟቋቋም የሚያስፈልጉ መመዘኛዎችን መሰረት አድርጎ የተመሰረተ ፓርቲ ነው።

በዚህም በአዲስ አበባና ድሬዳዋ እንዲሁም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ በሱማሌና ሐረር ክልሎች መንቀሳቀስ የሚያስችለውን ቁመና መፍጠር ችሏልም ብለዋል።

የማህበራዊ፣ የፖለቲካዊና የኢኮኖሚ ሴክተሮችና ለውጭ ጉዳይ ግንኙነት የሚያስፈልጉ አስፈላጊ ሰነዶችን ያዘጋጀና ፕሮግራም የቀረፀ ሲሆን ይህም ፓርቲው በአገሪቷ ሰላምና ብልጽግናን ለማምጣት ያስችለዋል ሲሉም አብራርተዋል።

በተለይም መልካም አስተዳደር፣ ግልጸኝነት፣ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ የብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋና ባህል እኩልነት፣ የአካበቢ ጥበቃ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ አገራት የባህል ትስሰር ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም