በትግራይ ክልል በምህንድስና ሙያ የተመረቁ ወጣቶች ተደራጅተው ሥራ ጀመሩ

55

መቀሌ መጋቢት 15/2011 በትግራይ ክልል በሲቪል ምህንድስና ሙያ የተመረቁ 800 ወጣቶች በሁሉ አቀፍ የገጠር ተደራሽ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሥራ ጀምረዋል።

የትግራይ ክልል ኮንስትራክሽን፣መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ እንዳስታወቀው ወጣቶቹ ሥራ የጀመሩት ተደራጅተው ለመሥራት ተስማምተው ባደረጉት እንቅስቃሴ ነው።

ወጣቶቹ  በክልሉ በመገንባት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በታማኝነትና በትጋት በመሥራት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በቢሮው የመንገድ ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ወልደገብርኤል ሃፍቱ ለኢዜአ  እንደገለጹት ወጣቶቹ  በሥራው የተሰማሩት 136 የገጠር ቀበሌዎችን በመንገድ ለማስተሳሰር እየተከናወኑ ባሉት ፕሮጀክቶች ውስጥ ነው።

በክልሉ መንግሥት 125 ሚሊዮን ብር የመደበላቸው መንገዶች 1 ሺህ 248 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚሸፍኑ ተናግረዋል።

ወጣቶቹ  እየተሳተፉ ያሉት በመንግሥት በጀትና በኅብረተሰቡ ጉልበት እየተሰሩ ባሉት ፕሮጀክቶች የአርሶ አደሮች ጉልበት እንዲያስተባብሩ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል።

ወጣቶቹ በአርሶ አደሩ ጉልበት የሚንቀሳቀሱ አነስተኛ ማሽነሪዎችን በመጠቀም ግንባታውን እያካሄዱ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣  የመንገዶቹን ጥራት የሚቆጣጠር 11 አባላት ያሉት አማካሪ ኮሚቴ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በግንባታው ከተሰማሩ የሲቪል ምህንድስና ባለሙያዎች መካከል አንዱ ወጣት ኤፍሬም ቸርነት የክልሉ መንግሥት ለእሱና ለጓደኞቹ  ያመቻቸላቸውን ሥራ በታማኝነትና በትጋት ለመሥራት እንዳነሳሳቸው ተናግሯል።

"ያለንን እውቀት ተጠቅመን ልምድ የምንቀስምበትና የራሳችንን ክህሎት አዳብረን በአደራ የተሰጠን ሥራ በጊዜ ለማጠናቀቅ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን" ብሏል።

ለወጣት ባለሙያዎች በተሰጠው ዕድል መደሰቱን የተናገረው ወጣት ዮሐንስ ዘነበ በበኩሉ ከሥራው ጋር በተያያዘ የሚገጥሙትን ችግሮች ተቋቁሞ በትጋትና በጥራት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የመንገድ ግንባታው አርሶ አደሩ ከአድካሚ የእግር ጉዞ ተላቅቆ ዘመናዊ የትራንሰፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚከፍትለት ተናግሯል።

ፕሮጀክቶቹ ለአካባቢው ኅብረተሰብ በክረምትና በበጋ ወቅት አገልግሎት በሚሰጥ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም