ኅብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ ከሚሰራጩ የጥላቻና የሐሰት መልዕክት ራሱን መጠበቅ አለበት-ምሁራን

53

መቱ መጋቢት 15/2011 ኅብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ ከሚሰራጩ የጥላቻና የሐሰት መልዕክት ራሱን በመጠበቅ አገራዊ ለውጡን ማስቀጠል እንደሚገባው አንዳንድ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን ተናገሩ።

ምሁራኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ሕዝቡ በማህበራዊ ሚዲያ  የሚለቀቀቁትን በተለይም አገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያስገባትን ለውጥ ለማኮላሸት የሚወጡ መረጃዎች እውነተኝነት ማረጋገጥ ያስፈልገዋል።

ለውጡ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ የሚዲያ ነጻነትን በማረጋገጥና  ኢኮኖሚው በማረጋጋት አገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገሩን አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጥላቻና የሐሰት መልዕክት ከአንድነት ይልቅ መለያየትን የሚሰብኩ፣ የአገሪቱን እድገትም ወደ ኋላ ስለሚመልሱ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህር ዶክተር ግርማ ገዛኸኝ እንዳሉት ከአገር ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅም የሚያስቀድሙ አካላት ሐሰተኛ መልዕክት በስፋት በማሰራጨት ኅብረተሰቡን ስጋት ውስጥ እየከተቱ ነው፡፡

የሚዲያ ነጻነትን ጨምሮ ለውጥ መመዝገባቸውን ያስረዱት ምሁሩ ፣ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንጻር የሚታዩትን ክፍተቶች በመሙላት መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

"በዓለም ላይ በርካታ አገራት የድንበር ጥያቄዎች ቢኖራቸውም ፤ ወደ ጦርነት የማስገባት እድላቸው ዝቅተኛ ናቸው" ያሉት ዶክተር ግርማ  በኢትዮጵያ በክልሎች መካከል የተፈጠረውን የወሰን ችግር በማራገብ ሕዝቡን ግጭት ውስጥ ለማስገባት የሚጥሩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው ብለዋል።

ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት  በተረጋገጠበት አገር አንዳንድ አካላት ግዴታቸውን ወደ ጎን በማድረግ አገርና ሕዝብን የሚጎዳ ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨታቸው ስጋት እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የመቱ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋሩማ አብዲሳ በበኩላቸው ሕዝቡ በፈለገበት ቦታና ሁኔታ ሀሳቡን በነጻነት መግለጹና መንግሥትን መተቸቱ የለውጡ ትሩፋት መሆኑን ያወሳሉ።

ሐሳብን በነጻነት በመጠቀም ረገድ  የሚታዩ ችግሮች ግን ኅብረተሰቡ የተሻለች አገር ለመፍጠር የያዘውን ጥረት ያደናቅፋል ብለዋል።

የመቱ ዩኒቨርሲቲ ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ሱሌይማን አብደላ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጥላቻ መልዕክትና ሐሰተኛ መረጃ ለውጡን ለመቀልበስ ካለመ እኩይ አመለካከት ስለሚመነጭ ጥንቃቄ ይደረግበት ባይ ናቸው፡፡

ኅብረተሰቡ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ በሆኑ ጥቂት ግለሰቦች የሚሰራጩትን አፍራሽ መልዕክት ማጣራት እንደሚገባውም መክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም