ግጭት ለህጻናት የቁም ገሀነም……..

180

ታዬ ለማ /ኢዜአ/ አብዛኛው አውስትራሊያዊ በየመን ምን እየተከሰተ እንደሆነ ላያወቅ ይችላል፡፡ በእርግጥ የመን የምትባለው አገር የት እንኳን እንዳለች የማያውቁም በርካቶች ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡

“አንድ ነገር ልላቸሁ እፈልጋለው፡፡ አውስትራሊያዊም ሆነ ሌላው የአለም ህዝብ በየመን እየደረሰ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እጅግ አሳዛኝና ዘግናኝ መሆኑን ሊያውቅ ይገባል።”  ይላል አውስትራሊያዊው ጋዜጠኛ ጃሰን ሊ በየመን ያለውን አስከፊ ሁኔታ በሚሰራበት በኤቢሲ ሚዲያ ለአውስትራሊያውያኑ ሲናገር፡፡

በየመን አምስት አመታትን የቆየው ጋዜጠኛው በዘገባው እንዲህ ይላል “ግጭት ጦርነት  በየመን እያደረሰ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ ክብደት ለመናገር ከኔ በላይ ማንም ምስክር መሆን አይችልም” ሲል ግጭት የሚያመጣውን የሰብዓዊ ቀውስ አስከፊነቱን ይመሰክራል ፡፡

ጦርነትና ግጭት አንድ አገርን  ብዙ ነገር ያሳጣል ያለው ጋዜጠኛው በአምስት አመት የየመን ቆይታው በርካታ ሰዎች ላይ ሊደርስ የማይገባ አሰቃቂና አስከፊ ነገሮች ማየቱንና  ብዙ ነገሮችም ሲጠፉ መመልከቱን ነው የተናገረው ፡፡

“ግጭት  ህጻናት ላይ የሚያደርሰው ሰብዓዊ ቀውስ ምን ያህል ጦርነት ለህጻናት የከፋ እንደሆነ ከምንም የበለጠ አይቻለው” ሲል የሰላም እጦትና ግጭት በከፋ ደረጃ ህጻናትን እንደሚጎዳ በዘገባው ያስረዳል፡፡

ጋዜጠኛ ጃሰን በየመን የሰላም እጦት ባስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ከተጠቁት የመናያዊያን መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህጻናት እንደሆኑ በመጥቀስ የመንያዊያን ለህጻናት ሲሉ ጦርነትን ማቆም እንደሚገባቸው ይሞግታል፡፡

እ.ኤ.አ 2015 በሁለት የፖለቲካ ቡድኖች መካከል የተፈጠረ የፖለቲካ ቀውስ ወደ ግጭት አድጎ የመን ለከፍተኛ ግጭት መዳረጎ ይታወቃል፡፡

በዓለማችን ካሉ ደሀ ሀገራት መካከል የምትመደመው የመን  ድህነቷ ላይ ጦርነቱ ተጨምሮበት አገሪቷን እንዳልነበረ እንዳደረጋት ቢቢሲ ጨምሮ የተለያዩ ሚዲያዎች አስነብበዋል፡፡

በተነሳው ግጭት  በርካታ የመናያዊያን  ህይወታቸው በአሰቃቂና በአሳዛኝ ሁኔታ ያለፈ ሲሆን ብዙዎቹ ቤት ንብረቴ ሳይሉ አገራቸውን ለቀው እግራቸው ወደ መራቸው አገር ለመሸሽ መገደዳቸውም  የአደባባይ ሚስጥር ነው።

የአለም አቀፉ የእርዳታ ድርጅት ሴፍ ዘ ቺልድረን በድህረ-ገጹ ጦርነት ህጻናት ላይ የሚያደርሰው  የስበዓዊ ቀውስ የማይታመን ነው ሲል የየመንን ጦርነት በማንሳት የአውስትራሊያዊውን ጋዜጠኛ  ሀሳብ ያጠናክራል፡፡

ጦርነቱ ህጻናት ላይ ብቻ የታወጀ እስኪመስል በየመን የሚገኙ ቁጥራቸው የበዛ ህጻናት መሞታቸውንና  ለሰብዓዊ ቀውስ መዳረጋቸውንም በድህረ ገጹ አስነብቧል።  እንደ ድህረገጹ መረጃ ከሆነ በየመን የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ከሰማንያ አምስት ሺ በላይ ህጻናት በምግብ እጦት ችግር መሞታቸውን ያትታል ፡፡

ይህ ማለት ይላል የተቋሙ መረጃ በእንግሊዝ በምትገኘው በርኒንጋሃም በምትባለው  ከተማ የሚገኙ ህጻናቶች በሙሉ ሞተዋል ሲል ግጭቱ ህጻናቱን ምን ያህል እንደቀጠፋቸው ያሳያል ይላል፡፡

የዩንሴፍ  መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ  በየመን ጦርነቱ ከተጀመረ ሶስት አመታት ብቻ በአለማችን ታይቶ የማይታወቅ የሰብዓዊ ቀውስ መከሰቱን አስታውቋል፡፡ አስራ አንድ ሚሊዮን ህጻናት ጦርነቱ ከተጀመረበት ግዜ ጀምሮ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለመፈለግ የተገደዱ መሆኑን በመጥቀስም የየመን ግጭት ህጻናትን የበለጠ የጎዳ መሆኑን ያመለክታል፡፡

በየመን በሁለት ኀይሎች መካከል የተነሳው ግጭት አስራ አንድ ሚሊዮን ህጻናትን  ለሰብዓዊ ድጋፍ ያጋለጠ ሲሆን አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ህዝቦችን ደግሞ ለኮሌራ ወረርሽኝ መዳረጉን የዩንሴፍ መረጃ ያሳያል፡፡

ጋዜጠኛው በኤቢሲ ባቀረበው ዘገባ በየመን የሚገኙ ህጻናት ኳስ እየተጫወቱ፤ እየቦረቁ እያሉ ድንገት በሚተኮስ ጥይት ህይወታቸው ያልፋል፤ ድንገት ከእናታቸው ከአባታቸው ጋር ሆነው ወደ አንድ ቦታ ሲሄዱ ላይመለሱ ይቀራሉ፡፡ ወደ ትምህርት ቤት እየተጎዙ እያለም አውቶብሳቸው ፈንድቶ የሚያሳዝን ሞት ይሞታሉ ይህ በህጻናቱ በየቀኑ የሚታይ አሳዛኝ ክሰተት ሲል ነው የገለጸው፡፡

ጋዜጠኛ ጃሰን ሊ  በየመን በቆየባቸው አምስት አመታት የህጻናት ሆስፒታሎችን  ጎብኝቷል።በጉብኝቱም በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ካገኛቸው የግጭቱ ሰለባዎች መካከል እስማኤል የሚባል የሰባት አመት ህጻን አንዱ  እንደ ሆነ ይገልጻል። እስማኤል  በሆስፒታሉም ሆኖ ጦርነት እጅግ  መጥፎ እንደሆነና  በጦርነት ማንም እንደማይተርፍ በመግለጽ  በየመንም ጦርነት እንዲቆም ፊላጎቱ እንደሆነ ለ ጋዜጠኛው ተናግሯል።

“ትምህርቴን ለመማር ወደ ትምህርት ቤት በምትወስደን አውቶብስ  እግሮቼን አስገባሁ፤ ከጓደኞቼ ጋር እየተጫወትኩ  እየተዝናናሁ ሲሄድ ድንገት ሳይታስብ ተኩስ ተከፈተ፡፡ አውቶብሳችንም ጉዳት ደረሰበት“ በማለት እስማኤል  አደጋው እንዴት እንደደረሰበት ለጋዜጠኛው ክስተቱን የተናገረው።  

እስማኤል ቦንብ የመታውን ገላ ለማገላበጥ እየሞከረ  ከፍንዳታው በኋላ የሆነውን እንደማያውቅና ከቀናት በኋላም እራሱን በሆስቲታል እንዳገኘው ይናገራል፤አጠገቡ የነበሩ ጓደኞቹም መሞታቸውንንና ማንንም ማግኘት እንዳልቻለም በሚያሳዝን አንደበት ይገልጽለታል።  

ኢማም ሌላዋ የመናዊ  የስድስት አመት ልጅ ነች። ኳስን ከዚህ ወደ እዛ ስታባርር በአየር ላይ በተተኮሰ ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ነች፡፡

“ነገ አስተማሪ ሆኜ አገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ፤ ግን ይህን ማድረግ የምችለው አገር ሰላም ሲሆን ብቻ ነው፡፡ አሁን የኔ  ምኞት በሀገሬ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ ብቻ ነው“ ስትል  ለጋዜጠኛው ህልሟን ያጫወተችው ሌላዋ ከጦርነቱ ሰለባዎች መካከል ነች፡፡  

ጦርነት ህጻናት ከመሞታቸው በተጨማሪ በስነልቦና በከፍተኛ ደረጃ እንዲጎዱ  በማድረግ ህልም እንዳይኖራቸው፤ ሰለ ነገ እንዳያልሙ ያደርጋቸዋል  ሲል  በዘገባው የሚናገረው አውስትራሊያዊ ጋዜጠኛ ጃሰን ይህንንም በየመን ቆይታዋው ሙሉ ለሙሉ ማረጋገጡን በልበ ሙሉነት ይናገራል ፡፡

ለቲአርቲ ወርልድ ድህረገጽ የየመን ግጭት ለህጻናት የቁም ገሀነም ሆኖባቸዋል ሲል የሚናገረው የዩንሴፍ ወኪል ሜርትስል ሲላኖ ከአስራ ስምንት አመት በታች የሆኑ 11 ሚሊዮን ህጻናት ለከፍተኛ ምግብ እጥረት፣ ለተለያዩ  በሽታዎች መጋለጥ፣ ለመፈናል ለሌሎች ማኀበራዊ አገልግሎቶች እጥረት ክፉኛ መጋለጣቸውን ጠቅሷል፡

መረጃው በትንሹ በየመን 1ነጥብ 8 ሚሊዮን ህጻናት ለረሀብ መጋለጣቸው፤ ከነዚህ ውስጥ ከአራት መቶ ሺ በላይ ለከፍተኛ ረሀብ የተጋለጡ መሆኑን በመጥቀስ ጦርነት ከማንም በላይ ለህጻናት የቁም ገሀነም ነው ሲል  አለም ፊቱን ወደ የመን እንዲያዞር ጥሪ አቅርቧል።

ኢል ቦስትኒ በስደተኞች ጉዳይ የምትሰራ ናት፤ግጭት ህጻናትን ለስደት የሚዳረግ መሆኑን ተከትሎ ኅጻናት በስደት ወቅት ከማንም የበለጠ መከራ እንደሚደርስባቸው ትናገራለች፡፡ ህጻናት በስደት ወቅት ከመንገድ መቅረት የታሰበበት ቦታ ያለመድረስ አብዛኛው ግዜ እጣ ፋንታቸው እንደሆነ በዩንሴፍ ድረ ገጽ ላይ ሀሳቧን አስፍራለች፡፡

የስደት ህይወትም ከትምህርታቸው ውጭ የሚያደርጋቸውና ምንም ምቾት የማይሰጣቸው እንደሆነ ታስረዳለች፡፡ በሊባኖስ የሚገኙ የሶርያ ስደተኞች እየደረሰባቸው ያለው ስቃይ ከፍተኛ እንደሆነ በመናገር ለሶርያ ስደተኛ ህጻናት ልንደርስላቸው ይገባል ስትልም አለም ፊቱን ወደ ሶሪያ እንዲያደርግ ትማጸናለች።

“ማንም ሰው ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ እንዲደርስ አይፈልግም፡፡ እነዚህ ህጻናት በብዙ ነገር አልፈዋል፡፡ ወደ ሊባኖስ ለመድረስ ብዙ ነገር አሳልፈዋል፡፡  ሞትን አይተዋል፡፡ ቦንብ ሲፈንዳ ተመልከተዋል። በአጠቃላይ መታየት የሌለባቸውን ሁሉ በዚህ ጨቅላ እድሜያቸው ተመልክተዋል” ስትል  በጦርነት ያዩትን ሰቆቃ በመግለጽ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ጠይቃለች።

“አሁን በሶርያ በግጭት ውስጥ ለሚገኙ ህጻናት ልንደርስላቸው የሚገባበት ሰዓት ነው፡፡ ስለ ነገ ተስፋቸው ማሰብ ይገባናል ፡፡ አሁን ትክክለኛው ግዜ ነው፤ ልጅነታቸው እንዲመለስ፤ እንደ ህጻናት  ቦርቀው እንዲያድጉ ሁኔታዎችን ልናመቻችላቸው ይገባል” ስትልም በሶርያ የሚገኙ ህጻናት በግጭት እያዩት ያለው መከራ እንዲያበቃ  ለአለም መልዕክቷን ታሰማለች፡፡

ልክ እንደ የመን ሁሉ  በምድረ ሶርያ በተነሳው አስከፊው ግጭት ከሰባት ሺ በላይ ህጻናት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡   አልጄዚራ ዩኒሴፍን ጠቅሶ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ  በሶርያ ግጭት ህጻናቶች  የማይገባቸውን ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡

እንደ አልጀዚራ ዘገባ በሶርያ ከሞቱት በተጨማሪ በርካታ ህጻናት ቀደም ብሎ የነበራቸው ህይወት በመበላሸቱ ከሞት ለማምለጥ ሲሉ  ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በሶርያ አንድ ሚሊዮን በላይ ህጻናት ጦርነት ያለ እናትና አባት አስቀርቷቸዋል በማለትም ዘገባው ይጠቅሳል።

ስደተኞቹ ቱርክ፣ ሊባኖስ፣ ጆርዳን እና ኢራቅን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ለመሰደድ የተገደዱ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያም መሰደዳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ከነበራቸው መልካም ኑሮ ግጭት ያፈናቀላቸው ህጻናት ከትምህርት ውጭም ሆነው የዕለት ምግባቸውን ለማግኘት እንደሚባክኑም የዩንሴፍ መረጃ ይጠቁማል፡፡

በስደት ህይወት የእለታዊ ምግብ ከመመገብ የዘለለ ማሰብ  ቅንጦት እንደሆነ የምትናገረው በስደት የምትኖር በደቡብ ድማስቆ የተወለደችው  በስደት የምትኖረው የዘጠኝ አመቷ ሙዞን አልመላን ተምራ ጋዜጠኛ መሆን ትፈልግ እንደ ነበር በመግለጽ አሁን ግን ምኞቷን ጦርነት እንደበላባት ለአርጄዚራ ታስረዳለች።

ደማስቆ ምርጥ ከተማ ነበረች የሚለው ደግሞ የአስራ አንድ አመቱ ባዳር አልታየር በዚህች ከተማ በመወለዴ እንደ እድለኛ እቆጥር ነበረ ይላል። እዚህ ያልተወለደ እድለ ቢስ አድርጎ እንደሚቆጥር ያስታውሰው ታዳጊው   አሁን ግን በደማስቆ መወለድ መረገም እንደሆነበት  እንባውን እያነባ በሊባኖስ ስደት ህይወት ላይ ሆኖ  ምሬቱን ለአርጄዚራ ይናገራል።

ጦርነቱ ልክ እንደ የመን ሁሉ ሶርያን ለከፍተኛ ስብዓዊ ቀውስ ዳርጎታል፡፡ በሶርያ እአአ በ2017 ብቻ የሰብዓዊ እርዳት የሚያስፈልጋቸው የህጻናት ቁጥር  ከ600ሺ ወደ 4.2 ሚሊዮን መድረሱና  ዘጠኝ መቶ አስር ህጻናት በዚህ አመት መሞታቸውን የዘጋርድያን ዘገባ ያመለከተው፡፡ 

ዩንሴፍ በጆርዳን አገር ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው 85 በመቶ ሶርያውያን በስደት በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላትም ደፋ ቀና የሚሉ መሆናቸውም ተጠቅሷል።

ማርክ ላውሮክ የተባለችው ሰብዓዊ መብት ጠበቃ ለአርጄዚራ እንደገለጸችው በሶርያ ተወልደው የሚያድጉ  ህጻናት አሰቃቂ ታሪክ በጣም የሚረብሸ እንደሆነ ተናግራለች፡፡

“የሶርያ ህጻናት ሰላም የናፈቃቸው ናቸው፡፡ ሰላም ምን እንደሆነ አያውቁትም ፡፡ እነሱ የሰላም ትርጉሙም የሚያውቁት አይመስልም፡፡ ምን ያድርጉ በጦርነት ውስጥ እየኖሩ” ስትል ሰቆቃቸውን አለም እንዲሰማው ትማጸናለች፡፡

"አሁን የህጻናት በጦርነት መሞት  በቃ ልንል ይገባል ፡፡ ጨዋታው መቀየር አለበት፤ ለአገሪቷ  ሰላም በማምጣት ህጻናቶች እንደልባቸው ሊቦርቁ ይገባልሲል በተባበሩት መንግስታት በጦርነት የሚገኙ ህጻናት ተጠሪ ቫርጂና ጋማባ በህጻናት ላይ የሚደርሰውን ግፍ እንዲቆም አለምን ቢጠይቁም አለም የሶርያን ህጻናት ሞት ሲያስቆም አልታየም፡፡ አሁንም በሶርያ ህጻናት ይሞታሉ፡፡

ሶርያና የመን ዛሬ እንደ ትላንቱ አይደሉም፡፡ ትላንትን እየናፈቁት ይገኛሉ፡፡ ትላንትን ግን ላይመለስ አልፎባቸዋል። አገራቸው ፈርሳባቸዋለች፡፡ የሞቱት ሞተዋል የተቀሩት ነገ  ህይወቴን አጣለው ብለው የሰቆቃ ኑሮን ይገፉታል፡፡ ሌሎች ደግሞ አገራቸውን ጥለው በስደት በተስፋ መቆረጥ ኑሮአቸውን በሰው አገር አድርገዋል፡፡

በሶርያም ሆነ በየመን  ለህጻናት መማር  አይታሰብም። እንደ ልብም ኳስን ከዚህ ወደ እዚያ እየመቱ መቦረቅ ብርቅ ሆኖባቸዋል። ምግብ ማግኘትም አሳሳቢ ነው፡፡  ጦርነትና ግጭት ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ይህን አስከፊ ነገር ትቶላቸው አልፏል ፡፡

በሁለተኛው አለም ጦርነት ህይወቱን ያጣው አሜሪካዊ ብሩስ ቮሪስ በአንድ ወቅት እንዲህ ስል ይገልጻል። ጦርነት የሰውን ህይወት ከመቅጠፍ እንዲሁም ንብረትን ከማውደም ውጭ ምንም ጥቅም ሊሰጥ አይችልም። ምናልባት ከጦርነት የሚገኘው ነገር ቢኖር ለቀጣይ ጦርነት ዘር መዝራት ብቻ ነው በማለት ነው የገለጸው።

በጦርነት ከጉዳት ይልቅ ምንም የምናገኘው ጥቅም ነገር ባለመኖሩ የነገ ተስፋ የሆኑ ህጻናት ቦርቀው እንዲያድጉና የተሻለች ሀገር እንዲወርሱ እኛ ኢትዮጵያኖችም ለሰላም ዘብ በመቆም በጋራ ድህነትን ማሸነፍ ብቸኛው አማራጫችን ሊሆን ይገባል። ግጭትና ጦርነት በታሪክ ለማንም ሲጠቅም አልታየምና፡፡ ሰላም! 

(በትርጉም የተሰራ)

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም