ብቁ አገር ተረካቢዎች እንድንሆን በአገር አቀፍ የምክክር መድረኮች ላይ በመሳተፍ ልምድ መቅሰም አለብን-ታዳጊ ተማሪዎች

54

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2011 ታዳጊዎችን ከወዲሁ ብቁ አገር ተረካቢዎች ለማድረግ በአገር አቀፍ የምክክር መድረኮች ላይ ማሳተፍ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተማሪዎች ገለፁ።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት "አዲስ ወግ" በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ ላይ ከእውቅ ፖለቲከኞችና ምሁራን በተጨማሪ ጥቂት ታዳጊ ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

በመሰል መድረኮች ላይ ታዳጊ ወጣቶችን መመልከት እምብዛም ያልተለመደ ከመሆኑ ጋር ታያይዞ ጅማሮው ይበል የሚያስብል ሲሆን፤ ኢዜአ "ከተሳተፋችሁበት መድረክ ምን ቀሰማችሁ" ሲል ከተማሪዎቹ መካከል አነጋግሯል።

ተማሪዎቹ በመድረኩ ላይ የተካሄደው ውይይትና የተነሱት ሀሳቦች ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል የሞራል ስንቅ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።

በቀጣይም ታዳጊ ወጣቶችን በመሰል መድረኮች የማሳተፉ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የእውቀት ለፍሬ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ሮቤል አለገሰ "ታላላቆቻችን ከሰሩት ተምረን ለአገራችን የበኩላችንን አሻራ እንድናስቀምጥ እኛ ታዳጊዎች በትልልቅ አገራዊ ምክክሮች ላይ መሳተፍ አለብን፤ ምክንያቱም አንዲህ ዓይነቱ መድረክ ትልቅ የእውቀት ምንጭም ነው" ሲል ይናገራል።

በውይይቱ ከተነሳው ሀሳብ  ለአገር አድገትም ሆነ ቀጣይነት ከመከፋፈል ይልቅ አንድነት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን መገንዘቧን የተናገረችው ደግሞ ከልደታ ማርያም የልጃገረዶች ትምህርት ቤት የመጣችው ተማሪ ኢትዮጵያ ሄሊ ናት።

ተማሪዋ ታታላቅ አገራዊ ጉዳቶች በሚነሱባቸውና የእውቀት ባለቤቶች በሚሳተፉባቸው እንዲሀ ዓይነቶቹ መድረኮች በተለይ አገር የመምራት ራዕይ ላላቸው ተማሪዎች ክፍት መሆን አለበት ትላለች።

የራዲካል አካዳሚ ተማሪ የሆነው ቅዱስ ዮሴፍ በበኩሉ የኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፈንታ በታዳጊዎች እጅ ላይ መሆኑን ጠቁሞ፤ ታዳጊዎችን በአገራዊ ምክከር ከማሳተፍ በዘለለ ለብቻቸው እንዲወያዩ መድረክ ሊዘጋጅላቸውም እንደሚገባ ተናግሯል።

የእውቀት ለፍሬ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችው ቃልኪዳን በላቸው በውይይቱ በፖለቲካው ሆነ በሌሎች ዘርፎች ብዙ የማታውቃቸውን ጉዳዮች የተመለከተ እውቀት መቅሰሟን አውስታለች።

በተለያዩ የውይይት መድረኮች ተማሪዎችን የመጋበዝ ልምድ ሊዳብር ይገባል ስትልም አሳስባለች።

"አዲስ ወግ" በሚል በተዘጋጀውና በኢትዮጵያ የአንድ ዓመት የለውጥ ሂደት ተስፋዎችና ፈተናዎች ላይ በመከረው ውይይት ላይ በአገሪቱ  የፖለቲካ፣ የምጣኔ ኃብትና ሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች ላይ  በምሁራኑና ፖለቲከኞቹ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም