ዴሞክራሲን መናገር እንጂ መተግበር ባለመቻሉ ችግሮች እየተከሰቱ ነው--- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

67

አዲስ አበባ  መጋቢት 14/2011  ዴሞክራሲን መናገር እንጂ መተግበር ባለመቻሉ በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች ምክንያት መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ   ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት "አዲስ ወግ" በሚል ርዕስ በተዘጋጀው አገራዊ መድረክ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ አሁን ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሰከነ ውይይት ያስፈልጋል ብለዋል።

መድረኩ በአደባባይ የሚወረወሩ ሃሳቦች የግጭት ምክንያት እንዳይሆኑ ወደ አዳራሽ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግና ከድንጋይና ዱላ ውርወራ የኃሳብ ፍጭት በማድረግ አገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አደባባይ ላይ ያለ ጀግንነት አገር የሚያፈርስ በመሆኑ ጉልበት እና ጊዜን ምጡቅ ኃሳብ በማመንጨት አሻጋሪ ኃሳቦች ሊፈልቁ እንደሚገባና ይህንንም አገር ለመገንባት መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

በዚህ ረገድም የፖለቲካ ልሂቃን፣ጋዜጠኞች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በእንደዚህ አይነት መድረክ ተገናኝተው መወያየታቸው አሻጋሪ ኃሳብ ለማፍለቅ እንደሚረዳም ጭምር ነው የገለፁት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ የተከማቸ ጥላቻ፣ ቂም አመጽ የነበረ በመሆኑ ይህንን አራግፎ መሻገር ካልተቻለ በአገሪቱ ህልውና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የራስን ቁስል ብቻ ማየት፣ ዋልታ ረገጥነት፣ ጊዜ ተረክነት ሙያ መናቅ፣ አቅላይነት፣ የመገናኛ ብዙሃን የተዛባ መረጃና ጠብ አጫሪ መረጃ እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሥነ-ምግባር መጓደል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያሉ ስብራቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዴሞክራሲን የሚናገር እንጂ  የሚተገብር ያለመኖሩ በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች ምክንያት እየሆነ መምጣቱንም አስምረውበታል።

መንግስት የተግባር ዴሞክራሲን ለማምጣት ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንና ለዚህም በአንድ ዓመት ውስጥ ጥሩ ጅምር ሥራዎች መሰራታቸውን አውስተዋል።

የሚዲያ አካላት የሚሰሩትን ሥራ ለጊዜያዊ ጥቅምና አድናቆት ለማግኘት ሳይሆን በታሪክ ሊወሳ በሚችል መልኩ በከፍተኛ ጥንቃቄና በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አሁን ላይ በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች መንግስት እያሳየ ያለው ትዕግስት ግድያና እስራት አሰልቺ በመሆኑን በመረዳት ሆኑን የጠቀሱት ዶክተር አብይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚገዳደር ከሆነ ግን መንግስት አይታገስም ብለዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መንግስት ጥሩ ሲሰራ በማመስገን መጥፎ ሲሰራ በመተቸት ከዚህ ውጪ ግን ህጋዊ ባልሆነ አካሄድ የባለ አደራ ምክር ቤት የሚል ድራማ ተቀባይነት እንደሌለው እና በምርጫ የሚፈልጉትን መሪ መምረጥ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማትን በተመለከተ ቻይና እና መካከለኛው ምስራቅ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን የገለፁት ዶክር አብይ ኢትዮጵያዊያንም የራሳቸው ኢንቨስትመንት በመሆኑ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በዓለም ላይ በተምሳሌትነት የሚወሰዱ ሰዎች ያላቸውን የሰጡ ሰዎች በመሆናቸው ኢትዮጵያዊያንም ይህንኑ በመገንዘብ በነፃ ማገልገልንና መስጠትን መልመድ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የውጪ ግንኙነትን የህገ መንግስት ማሻሻያን በሚመለከት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ኃሳቦች እንዲደመጡ እና በሰከነ ውይይት መፍትሄ ማፈላለግ ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም