የኢንዱስትሪያል አክሲዮን ማህበሩ ለክልሉ ህዝብ ልማት የሚያደርገውን ጥረት መንግስት ይደግፋል--- ዶክተር አምባቸው

70

ባህርዳር መጋቢት14/2011 የአባይ ኢንዱስትሪያል አክሲዮን ማህበር አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት የአማራን ህዝብ ለመጥቀም የሚያደርገው ጥረት የክልሉ መንግስት እንደሚደግፍ ርዕሰ መስተዳደር  ዶክተር አምባቸው መኮንን አስታወቀ፡፡

አክሲዮን ማህበሩ ሁለተኛ ጉባኤውን  ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አካሄዷል፡፡

በጉበኤው ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳደሩ " የክልሉን ጥሬ ሃብትና የሰው ጉልበት አቀናጅቶ የሚጠቀም ጠንካራና ዘላቂ ኢንዱስትሪ እጥረት አለ" ብለዋል፡፡

በክልሉ በተደራጀ አቅም ታላላቅ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

" አባይ ኢንዱስትሪያል አክሲዮን ማህበርን  የአማራ ወጣት ከመንግስት ባልተናነሰ  ለስራ እድል ፈጠራ በጉጉት የሚጠብቀው ተስፋው ነው" ብለዋል፡፡

አክሲዮን ማህበር ውጤታማ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደሚያድርግ ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ሀብትን፣ ጉልበትን፣ እውቀትንና ልምድን በማስተባበር  ወደ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት ለማሸጋገር አክሲዮን ማህበሩ ፈር ቀዳጅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

መንግስትና ባለሃብቱ ተቀናጅተው የአካባቢውን ጥሬ ሃብት በመጠቀም ጠንካራ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም የተጀመረው ጥረት እንደ ሃገር አቀፍም ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"በዚህም ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት ከዳር እስከ ዳር ሃገራዊና ክልላዊ አቅምን ማጎልበት ያስችላሉ ብለዋል፡፡

የአክሲዮን ማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል ማህበሩ የአማራን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አዋጭ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የማህበሩን አቅም ለማጠናከር ባደረገው  እንቅስቃሴ ከአባላት ከአንድ ቢሊዮን 300 ሚሊዮን  ብር በላይ የመዋጮ ገንዘብ መሰብሰብ እንደተቻለ አመለክተዋል፡፡

በዚህም የሲሚንቶ፣ የብረታብረት፣የስኳር፣ የጨርቃጨርቅ እና ሌሎችንም ፋብሪካዎችን ለማስገንባት ረጅም ርቀት መጓዝ መቻሉን አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡

ለፋብሪካዎች የግንባታ ቦታ ከሦስተኛ ወገን ነፃ የማድረግ፣ መብራት፣ ውሃ፣ መንገድና ሌሎችንም መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ግንባታቸው የተጀመሩና በሂደት ላይ የሚገኙ እንዳሉ አመልክተዋል፡፡

አባይ ኢንዱትሪያል አክሲዮን ማህበር  16 ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት በመንግስት፣ በባለሃብትና በልማት ድርጅቶች ትብብር እየሰራ ይገኛል ተብሏል፡፡

ጉባኤው የአክሲዮን ማህበሩን 2010 የስራ ዘመን  አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን የኦዲት ሪፖርት መርምሮ በማጽደቅ ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም