ለውጡ የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋ ቢሆንም ፖለቲከኞች በለውጡ ልክ እየተንቀሳቀሱ አይደለም --- አስተያየት ሰጪዎች

134

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2011 በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ሂደት የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋ ቢሆንም ፖለቲከኞች በለውጡ ልክ እየተንቀሳቀሱ እንዳልሆነ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ። 

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት "አዲስ ወግ" በሚል ርዕስ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉት የቀድሞ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ግርማ ሰይፉ እንዳሉት፤ ለውጡ ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ፖለቲከኞች የመጫወቻ ምህዳሩን በአግባቡ በመጠቀም ለውጡን ለማስቀጠል ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።     

በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች ከፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ጋር በተያያዘ እንደሆነ የገለጹት አቶ ግርማ ጥያቄዎቹ ግን ወቅታዊ አይደሉም ብለዋል።

  ከውይይት ተሳታፊ ዶክተር ተስፋዬ ካሳ በበኩላቸው የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ምሁራንና ዜጎች ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

እንደ ዶክተር ተስፋዬ ገለጻ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የነበሩ መሪዎች በኃይልና በጦርነት አገር የያዙ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሚከተሉት መንገድ ግን ከዚህ ሁሉ ውጭ ነው።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የመንግስት ለውጥ ከተደረገባቸው ጊዜያት ውስጥ በአሁኑ ወቅት ያለው ለውጥ ከውስጥ የመነጨ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።    

የፖለቲካ ፓርቲዎች በተፈጠረው የፖለቲካ ምህዳር በመጠቀም ለውጡ ወደፊት እንዲቀጥል ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ግርማ በገዢው ፓርቲ ስንፍና ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገቢውን ስራ ሳይሰሩ ቢቀር ለውጡ ሊቀለበስ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

 የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተመራማሪ ዶክተር ዲማ ነገዎ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ለውጥ ተግዳሮቶች ያሉበት ቢሆንም ሊቀለበስ እንደማይችል ገልጸዋል።

ከለውጡ ጋር በተያያዘ ከውስጥ የሚታዩ ተግዳሮቶች አደገኛ እንደሆኑ የገለጹት ዶክተር ዲማ እነዚህ ተግዳሮቶች መፍታት ላይ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ዲማ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ያለው ለውጥ ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ የነበሩ የዴሞክራሲ፣ የመብት፣ የብሔርና የቋንቋ ጥያቄዎች ሲንከባለሉ የመጡ ናቸው።

የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ከገዢው ፓርቲ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ የገለጹት ዶክተር ዲማ ከለውጡ ጋር በተያያ በፓርቲው ውስጥ የሚታየውን ተግዳሮት እልባት ማግኘት አለበት ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤትትናንት በተጀመረውየውይይት መድረክ "የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ ታሪካዊ ዳራና ወቅታዊ ተግዳሮት" እንዲሁም ''የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የአፍሪካ ተሳትፎ'' በሚሉ ርዕስ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል። 

የውይይት መድረኩ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን ''የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት፣ የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ ሥራ ፈጠራና ማህበራዊ አካታችነት'' እንዲሁም ''የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ማጽናት በኢትዮጵያ፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አካሄዶች'' በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲካሄድ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም