የፍርድ ቤቶችን ስልጣን የሚሸረሽሩ ህጎች ተገቢ ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ

74

አዲስ አበባ  መጋቢት 14/2011 በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የፍርድ ቤቶችን ስልጣን የሚሸረሽሩ ህጎች ተገቢ ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 684/2002 ዳኞች ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ የሚያስችል ብቁ አዋጅ አይደለምም ተብሏል።

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ሥርዓት ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት እንደገና በሚቋቋመው የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

የዳኝነት ሥርዓት ማሻሻያ ጉባኤ አባልና የረቂቅ አዋጁ አቅራቢ አቶ ማንደፍሮት በላይ እንዳሉት አዲሱ ረቂቅ ሰነድ ከነባሩ አዋጅ በተሻለ ህገ መንግስቱን ተከትሎ የሚሻሻል ነው።

ነባሩ አዋጅ ቁጥር 684/2002 ስር 18 አንቀፆች ብቻ የተካተቱበት ሲሆን አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ግን ከ40 በላይ አንቀጾችን ያካተተ መሆኑ ተነግሯል።

ዳኞች በአስተዳደር ጉባኤው ስለሚኖራቸው አባልነት ሁኔታ የእድሜና የፆታ ስብጥር እንዲሁም የአገልግሎት ጊዜና ስንብት በረቂቅ አዋጁ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ በኢትዮጵያ የዳኞችን ስልጣን የሚሸረሽሩ ህጎች  በተለያዩ አካላት እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች ብሎም የፌዴራል መንግስቱ ዳኞች ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዳይሰሩ የሚያደርጉ ህጎችን በተደጋጋሚ ያወጣሉ ብለዋል።

በመሆኑም ሶስተኛው የመንግስት አካል የሆነውን የዳኝነት አካል ሥልጣን የሚጋፉ ህጎች እንዳይወጡ የሚከለክል አንቀጽ በአዋጁ መካተት አለበት ነው ያሉት።

በተጨማሪም አስፈላጊነቱ ታይቶ ካልሆነ በስተቀር የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ዳኞች በያዙት መዝገብ ላይ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት የሚገልጽ አንቀጽ ሊኖር ይገባል ብለዋል።

የህግ ባለሙያና ጠበቃ አምሃ መኮንን እንዳሉትም ዳኞች መብትና ጥቅማቸውን ማስከበር እንዲችሉ የዳኞች ማህበር መመስረት ወቅታዊና ተገቢ ነው።

ነገር ግን የዳኞች ማህበር ሲመሰረት በአዋጅ መብታቸውና ጥቅማቸውን ከሚያስከብሩበት አሰራር ውጭ ምን አዲስ አላማ ሊኖረው እንደሚችል መብራራት ይኖርበታል ብለዋል።

በወንጀል ተከሰው በጥበቃ ላይ እያሉ በአያያዝ ጉድለት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈፀምባቸውን እስረኞች በተመለከተ ዳኞች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም