አብዛኛው አርሶ አደር አሁንም የምግብ ዋስትናውን አላረጋገጠም

78

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2011 አብዛኛው የኢትዮጵያ አርሶ አደር አሁንም የምግብ ዋስትናውን እንዳላረጋገጠ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያን ገበሬ ተጨባጭ ሁኔታ ማዕከል ያደረገ አዲስ የገጠር ፖሊሲ ሊዘጋጅ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት "አዲስ ወግ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው አገራዊ መድረክ በዛሬው የሁለተኛ ቀን ውሎ 'በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብትና የስራ ዕድል ፈጠራ' ዙሪያ ምክክር አድርጓል።

በመድረኩ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ረዲ አሊ፤ የመሬት ስሪት ተመራማሪና የጥናት ባለሙያ አቶ ደሳለኝ ራህመቶ፣ የህብረት ባንክ የቦርድ ሊቀ-መንበርና የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያው አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ ዛፉ እና ወይዘሮ ብርሃኔ አስፋው በርዕሰ ጉዳዩ የመወያያ መነሻ ሃሳብ የሚሆን ሙያዊ ምልከታቸውን አቅርበዋል።

አቶ ደሳለኝ ራህማቶ የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍን በሚመለከት "ባለፉት ዓመታት መንግስት መሰረተ ልማትን በገጠር ተደራሽ ለማድረግ ባከናወናቸው ተግባራት አገራዊ ዕድገት እንዲመዘገብ አውንታዊ ሚና ተጫውቷል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ነገር ግን የአገሪቱ ግብርና አሁንም ድረስ 'የዝናብ እስረኛ' መሆኑን ጠቁመው፤ "ይህም ዋነኛ የምግብ አምራች የሆነው የህብረተሰብ ክፍል የምግብ ዋስትና እንዳይኖረው አድርጓል" ብለዋል። 

ለማብራሪያቸውም በሴፍቲኔት የታቀፉና በአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚኖሩ ገበሬዎችን ቁጥር ለአብነት አንስተዋል።

በዘርፉ እስካሁን ተመዘገቡ የሚባሉ ስኬቶችም ቢሆኑ ሩቅ በማያሻገርና በተውሶ በመጡ ልምዶች መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አንጻር በተጨባጭ የኢትዮጵያን ገበሬ ያማከለ አዲስ የገጠር ፖሊሲ ሊቀረጽ ይገባል ነው ያሉት።

ዶክተር ረዲ አሊ በበኩላቸው በኢንቨስትመንት የተፈጠረውን ገቢ ግብርናው ያለውን ተጨባጭ አቅም ለማጎልበት አለመሰራቱን ይናገራሉ። 

ይህም ገበሬው በየ10 ዓመቱ የሚከሰትበትን ድርቅ ከ10 ዓመት በፊት የነበረውን አቅም ይዞ እንዲጠብቀው አድርጓል ነው ያሉት።

ግብርናውን በፍጥነት ለማሻገር ከተፈለገ በዘርፉ ያሉ አቅሞች ላይ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ በመምከር።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ፖለቲካውን የምትመራበት ግልጽ መስመር ቢኖራትም፤ የኢኮኖሚውን መዳረሻ የሚያሳይ ግልጽ ፖሊሲ በማቅረብ ረገድ ውስንነት እንዳለባት የተናገሩት ደግሞ አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ናቸው።

የፋይናንስ ዘርፉ አሁንም ድረስ በመንግስት ዳፋ ስር በመሆኑ እንደፈለገ ተንቀሳቅሶ ለዜጎች ስራ መፍጠር አለመቻሉንም አብራርተዋል።

ወይዘሮ ብርሃኔ አስፋው "የታክስ ዘርፍና የኢንቨስትመንት ደንብ ግልጽና አሰሪ ባለመሆኑ ትርፍ ሃብት ያላቸው የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት በሚፈለገው ልክ እንዳይሳተፉ አድርጓል" ይላሉ።

የሰራተኞች የጡረታ ፈንድን በባንክ ከማከማቸት ይልቅ ለዜጎች ስራ መፍጠር በሚያስችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ መዋል እንዳለባቸውም መክረዋል።

ውይይቱ ዛሬ ፍጻሜውን የሚያገኝ ሲሆን በዛሬው የከሰዓት በኋላ መድረክ "የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ፣ ማጽናት፣ ተግዳሮቶችና የቀጣይ አቅጣጫዎች" በሚል ርዕስ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም