አየር መንገዱ ከሰሞኑ የውጭ መገናኛ ብዙሃን እየጻፉ ያወጡት ዘገባ ትኩረት ለማሳት የሚደረግ ሙከራ ነው አለ

113

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኒውዮርክ ታይምስና ዋሽንግተን ፖስት አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን አብራሪ ''የማክስ 8 ምስለ-በረራ ስልጠና አልወሰደም'' በማለት ያወጡትን ዘገባ ሀሰትና የጉዳዩን ዋና ትኩረት ለማሳት የሚደረግ ሙከራ ነው አለ።

በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ድረ-ገፅ ላይ ''የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማክስ 8 ምስለ-በረራ (ሲሙሌተር) ነበረው አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን አብራሪ ግን ስልጠናውን አልወሰደም'' የሚል ዘገባ መውጣቱ ይታወሳል።

በተመሳሳይ ዋሽንግተን ፖስትም አብራሪው ''የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማክስ 8 ምስለ-በረራ ስልጠና አልወሰደም'' በሚል ተመሳሳይ ዘገባ አሰራጭቷል።

አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫም የሰባት ምስለ በረራ (ሲሙሌተር) ባለቤት መሆኑንና አብራሪዎች በየጊዜው በቂ ስልጠና እንደሚያገኙ ገልጿል።

በዚሁ አግባብም ዋና አብራሪው በቦይንግ አውሮፕላን አምራች ኩባንያና በአሜሪካ የአቪዬሽን አስተዳደር የተቀመጡ የበረራ ስልጠናዎችን እና ከወራት በፊት በኢንዶኔዥያ በደረሰው ተመሳሳይ የአውሮፕላን አደጋ ጋር በተያያዘ ስለ አደጋ ጊዜ የበረራ መመሪያ በቂ ግንዛቤ አለው ነው ያለው።

ካልታወቁ አካላት ተገኘ የተባለ መረጃም ምንም ማስረጃ የሌለው ስም ማጥፋት መሆኑንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከበረራ የታገደውን የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ትኩረቱ ለማስቀየር የተደረገ ጥረት መሆኑን ገልጿል።

በመሆኑም አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ብቁ የሆኑ ኪው 400፣ ቢ737 ኤን ጂ፣ ቢ 737 ማክስ፣ ቢ 767 ፣ ቢ 787 ፣ ቢ 777 እና ኤ 350 የተባሉ ሰባት ምስለ በረራዎች እንዳሉት አስታውቋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአፍሪካ ከተሟላ የስልጠና መሳሪያ ጋር በቂ ስልጠና ከሚሰጡት ጥቂት ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑንም ነው አየር መንገዱ የገለጸው።

ጋዜጦቹም በማስረጃ አልባነት የጻፉትን በመሰረዝ እውነታውን ማሳወቅ እንደሚኖርባቸውና አየር መንገዱን ይቅርታ ሊጠይቁ እንደሚገባም አስገንዝቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም