ዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ ግንኙነቱን እንዲያጠናክር የድርሻችንን እንወጣለን--- ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች

110

መቱ  መጋቢት 14/2011 መቱ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እና በጥናትና ምርምር ተቋማዊ ግንኙነቱን እንዲያጠናክር የሚጠበቅባቸውን አስተዋጾ እንደሚያበረክቱ  ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች ገለጹ፡፡

"ዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ ግንኙነትን ለማጠናከር የምሁራን ሚና " በሚል መርህ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ከመጡ ምሁራንና ታወቂ ግለሰቦች ጋር መክሯል።

በመድረኩ የተሳተፉ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች  እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የተመሰረተበት ጊዜ ቅርብ በመሆኑ ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት አነስተኛ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ዶክተር ግርማ ገዛሀኝ እንደገለፁት በዩኒቨርሲቲዎቹና በስራቸው ባሉ የትምህርት ክፍሎች መካከል ትስስርና መደጋገፍ እንዲፈጠር የድርሻቸውን ይወጣሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃም በትምህርት ዙሪያ ከሚሰሩ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር ዩኒቨርሲቲውን ለማቀራረብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።

ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ በበኩላቸው የመቱ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበት አካባቢ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገና  ለግብርና አመቺ መሆኑን ገልጸዋል።

አካባቢው በተለይም በማር፣ ቡናና ቅመማ ቅመም አምራችነቱ ታዋቂ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ዩኒቨርሲቲው በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ግብርና ዘርፎች ከሀገር ውስጥና ከውጭ ተቋማት ጋር ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በትብብር ማካሄድ የሚችልባቸውን እድሎች መፍጠር ያስፈልጋል" ብለዋል ።

"አካባቢውን የማስተዋወቅና ዩኒቨርሲቲውን ከተቋማት ጋር ማቀራረብ ከምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች ይጠበቃል" ያሉት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ እርሳቸውም በእዚህ በኩል የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል ።

ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ውጤታማ ስራ እንዲሰራ አምባሳደር ሆነው እንደሚያስተዋውቁም ቃል ገብተዋል ።

የመቱ ዩኒቨርሲቲ ድህረ ምረቃ ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር አቶ ሱሌይማን አብደላ በበኩላቸው ለትምህርትና ስልጠና ወደ ውጭ ሀገራት የሚሄዱ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ዩኒቨርሲቲውን የማስተዋወቅና ከተቋማት ጋር ግንኙነት እንዲኖረው ሚናቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ተቋሙ ከአዲስ አበባ፣ ጅማና ወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትብብር በመፍጠር የልምድ ልውወጥ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የመቱ ዩኒቨርሲቲ ልማትና አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋሩማ አብዲሳ በበኩላቸው "በተለያዩ የሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስተምሩ የአካባቢው ተወላጅ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች ባሉበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቋሙን እንዲያስተዋውቁ በማሰብ የውይይት መድረኩ የዘጋጅቷል" ብለዋል ።

ምሁራኑና ታዋቂ ግለሰቦቹ በዩኒቨርሲቲው የተቋማዊ ግንኙነት መጠናከር አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የጋራ ግንዛቤና መግባባት መፍጠርም የመድረኩ ዓላማ መሆኑን አብራርተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ አጭር ጊዜ በመሆኑ በተለያዩ ተቋማት ልምድ ያካበቱ ምሁራን ልምዶቻቸውን እንዲያካፍሉና እገዛ እንዲያደርጉም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመቱ ዩኒቨርሲቲ ትናንት በተካሄደው የምክክር መድረክ በሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተቋማት የሚሰሩ የአካባቢው ተወላጅ ምሁራን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦች ተሳትፈዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ከ7 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎችን በመጀመርያና በሁለተኛ ዲግሪ በማስተማር ላይ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም