ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛና በሦስተኛ ድግሪ አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ሊከፍት ነው

84

ሶዶ መጋቢት 14/2011 ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ድግሪ አምስት አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ሊከፍት ነው፡፡

ተቋሙ አዲስ ለሚከፍታቸው የትምህርት መርሀ ግብሮች በቀረጻቸው ሥርአተ ትምህርቶች ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመጡ ምሁራን ጋር ትናንት መክሯል።

በዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ተባባሪ ዲን ዶክተር ወንድሜነህ ታዬ በእዚህ ውቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ጀምሮ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት የሀገሪቱን ዕድገትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማፋጠን እየሰራ ነው፡፡

በዚህ ሂደትም በየጊዜው የሀገሪቱንና የገበያውን ወቅታዊ ፍላጎት መነሻ በማድረግ አዳዲስና ተመራጭ የትምህርት መርሀ ግብሮችን መክፈቱን አስታውሰዋል።

እንደ ዶክተር ወንድሜነህ ገለጻ በቀጣይ ዓመት አዲስ የሚከፈቱት የትምህርት መርሀ ግብሮች ትኩረት ያደረጉት በግብርና፣ በጤናና ማህበራዊ ሳይንስ ዘርፎች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡

የግብርና ምጣኔ ሃብትና የማህበረሰብ ጤና ዩኒቨርሲቲው በሦስተኛ ድግሪ አዲስ የሚከፍታቸው ሲሆን በቀጣይ ዓመት ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ይጀምራል።

ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛ ዲግሪ የሚከፍታቸው በወላይትኛ ቋንቋ፣ በታርክና ቅርስ ጥበቃ እና በልማት አስተዳደር የትምህርት መርሀ ግብሮች መሆኑንም ዶክተር ወንድሜነህ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ወንድሙ ወልደ በበኩላቸው እንደተናገሩት ከጉባኤው የሚገኘው ግብአት የተዘጋጀው ሥርአተ ትምህርት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግና ለውጤታማነት አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው፡፡

አዲሶቹ የትምህርት መርሀ ግብሮች ተግባራዊ ሲደረጉ የህዝቡን ጥያቄ በቅርበት ለመፍታት ይረዳሉ ያሉት ዶክተር ወንድሙ በሁለተኛ ዲግሪ የሚከፈቱት የዩኒቨርሲቲውን ዋና ካምፓስ ጨምሮ በዳውሮ ታርጫ፣ በኦቶና፣ በሃላባና በዱራሜ ሳይቶች እንደሚሰጡ አመለክተዋል።

"አዳዲስ የሚከፈቱት መርሀግብሮች ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛ ድግሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት መርሀ ግብሮች ወደ 47 እንዲሁም በሦስተኛ ዲግሪ የሚሰጣቸውን ወደ አራት ከፍ ያደርጉታል" ብለዋል፡፡

ከወቅቱ ገበያ ጋር የሚሄድ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል የጀመረውን ትኩረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር ውንድሙ አመልክተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በድህረ ምረቃ ትምህርት ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በቀን፣ በዕረፍት ቀናትና በክረምት መርሃ ግብር ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ መሆኑን ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም