ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የግብር አምባሳደሮች ጥሪ አቀረቡ

55

አዳማ  መጋቢት 14/2011 ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ራሱን ብሎም ሀገሪቱን ለመጥቀም ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ  የግብር አምባሳደሮች ጥሪ አቀረቡ፡፡

በኦሮሚያ  ለአንድ ዓመት የሚቆይ  የገቢ ግብርና ታክስ ንቅናቄ ዛሬ በአዳማ ይፋ በተደረገበት ስነስርዓት የክልሉ መንግስት ፕሬዝደንት  አቶ ለማ መገርሳ  ከአትሌቶች፣ አርቲስቶችና የኃይማኖት አባቶች የተወጣጡ ታዋቂ ሰዎችን በግብር አምባሳደርነት ሾመዋል፡፡

ከተሿሚዎች መካከል ቀሲስ በላይ መኮንን በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ግብር እና ታክስን  ከማጭበርበር ነፃ ሆኖ  መክፈል ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ  ልማትና እድገት ሚናው የጎላ ነው።

" ለልማት የሚውል ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ ካልተቻለ  የህዝቡን ጥያቄ ስለማይመለስ በንቅናቄው ሁላችንም የድርሻችን ልወጣ ይገባል "ብሏል።

ህዝቡ ግብር እና ታክስ መክፈል ባህሉ አድርጎ  ለሀገር ልማትና እድገት ቀጣይነት ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋንያን  መሆን እንዳለባት ያመለከተው ደግሞ ሌላው የግብር አምባሳደር አርቲስት አጫሉ ሁንዴሳ ነው።

"  ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ከክልሉ መንግስት ጎን ሆነን በተሻለ መልኩ በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል"  ብሏል።

ኮለኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ከህብረተሰቡ የሚነሳውን የመጠጥ ውሃ ፣ መብራት ፣ ጤና ፣ትምህርትና የመንገድ መሰረተ ልማት ለማሟላት ገቢውን በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ ገልጻለች።

የክልሉ መንግስት ንቅናቄውን ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የድርሻዋን እንድትወጣ የተሰጣትን የግብር አምባሳደርነት ሹመት በመቀበል ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።

ሌላው የግብር አምባሳደር ጋዜጠኛ ጃፋር አሊ በሰጠጠው አስተያየት ህዝቡ አሁን የሚፈልገውን ልማት ለማስቀጠል ገቢ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሶ የግብር ከፋዮች ግንዛቤን በማሳደግ ለንቅናቄው መሳካት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግሯል።

ግብር መክፈል የስልጣኔ ምልክት መሆኑን ያመለከተው  ጋዜጠኛ ጃፋር አሊ"  በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየውን የተሳሳተ አመለካከት ለማረም ሁላችንም በትብብር መስራት ይጠበቅብናል "ብለዋል።

ክልሉ  ብሎም ሀገሪቱ ከኋላ ቀርነት መላቀቅ የሚችሉ  በልማትና እድገት በመሆኑ ሊዚህም የሚያስፈልገው የገቢ ግብር አሰባሰብ ላይ አቅምን አሟጦ መጠቀም እንደሚገባም አመልክቷል፡፡

ግብር ከፋዩ ሀብረተሰብ ለራሱ ብሎም ለሀገሩ ልማት የሚውለው ገቢ በወቅቱ ተግባራዊ በማድረግ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የግብር አምባሳደሮች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም