የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለው ዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት በአደጋው ምክንያት አይቀንስም- ባለሙያዎች

183

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2011 በቅርቡ የደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተቀባይነት እንደማይጎዳው የአቪዬሽን ባለሙያዎች ተናገሩ።

አየር መንገዱም ከሰሞኑ በኒውዮርክ ታይምስና ዋሽንግተን ፖስት እየወጡ ያሉ ዘገባዎች ሀሰትና የጉዳዩን ዋና ትኩረት ለማሳት የሚደረጉ ሙከራዎች ናቸው ብሏል።

ስጋቶችን መቀነስ እንጂ ማጥፋት ባለመቻሉ ከስጋትና ከአደጋ ነጻ የሆነ ኢንዱስትሪ የለም።

አስተማማኝ በሚባለው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪም አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮች ከፍተኛ ዋጋ በማስከፈላቸው "የአቪዬሽን ደህንነት በደም ይጻፋል" ይባላል።

በቅርቡም ዓለም ያዘነበትና በኢትዮጵያ የተከሰተውም ይኸው ነው።

ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ይበር የነበረ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ተከስክሶ 157 ሰዎች ህይወታቸውን አጡ።

የ35 አገራት ዜጎች ህይወታቸውን ያጡበት አደጋ እጅግ አሳዛኝና ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ቢሆንም ሌላው ዓለም ለደህንነቱ ጥንቃቄ የወሰደበት ሆነ።

አምራቿን አገር አሜሪካ ጨምሮ ከ40 በላይ አገራት አየር መንገዶች ጉዳዩ እስኪጣራ ለጊዜው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ሲያግዱ የአውሮፓ ህብረትም በአህጉሪቱ የአየር ክልል እንዳይበር ጭምር ከልክሏል።

በዚህና አውሮፕላን ያዘዙ አየር መንገዶች ትእዛዛቸውን በመሰረዛቸው ቦይንግ ኩባንያ ትልቅ ጫናና አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በፊት ተመሳሳይ አደጋ የደረሰበት የኢንዶኔዥያ አውሮፕላን አንዱ የምርመራ ውጤት ቦይንግ በማክስ 8 አውሮፕላን ላይ ያደረገውን ማሻሻያ አብራሪዎች ሊረዱትና ጥንቃቄ ሊያደርጉበት በሚችል መንገድ በግልጽ በመመሪያ አለማካተቱ ነው።

ምንም እንኳን የኢትዮጵያው አደጋ የምርመራው ውጤት ገና ይፋ ባይሆንም "አዲስ ቴክኖሎጂ አዲስ ችግርና አዲስ መፍትሄ ይዞ ይመጣል" እንደሚባለው የተወሰዱ እርምጃዎች የሚያመላክቱት ቴክኖሎጂው ሊኖረበት የሚችለውን ክፍተት ነው።

በኢትዮጵያ ላይ የደረሰው አውሮፕላን አደጋ ለሌሎች የጥንቃቄ መልእክት መሆኑን ያስረዱት ዮናታን መንክር ካሳ (የኤሮሪድ አቪዬሽን ሚዲያ ዋና ስራ አስፈጻሚና የግል አውሮፕላን አብራሪ) ናቸው፡፡

ከአደጋው በኋላ የዓለማችን ታዋቂ ሰዎች፣ የአቪዬሽን ባለሙያዎች፣ ስለ ኢትዮጵያ መልካም ተናግረው የማያውቁ የዓለም መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ጭምር ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ በጎ በጎውን ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በተለይም የሲ ኤን ኤን ጋዜጠኛ ሪቻርድ ኩዌስት የኢትዮጵያ አየር መንገድ "በሌላ አገር አየር መንገድ ለመሄድ ፍርሃት ሲያድርባችሁ የሚመረጥ ነው" ማለት የሰጠው ምስክርነት የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።

ዓለም ይህን ያህል በአየር መንገዱ እንዲተማመን የሆነው አንድ ደሃ አገር ሃብታም አገራት መመስረት ያልቻሉትን ብቁ አየር መንገድ መመስረት በመቻሏ ነው።

ዮናታን መንክር ካሳ (የኤሮሪድ አቪዬሽን ሚዲያ ዋና ስራ አስፈጻሚና የግል አውሮፕላን አብራሪ)"ለሆቴሎች አምስት ኮከብ የመጨረሻው እንደሆነ በአየር መንገድም አምስት ኮከብ አለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለ አራት ኮከብ ነው። በአፍሪካ ውስጥ አቻ የሌለው በቅርብ ርቀት እንኳን የሚወዳደረው አየር መንገድ የለም። በአውሮፕላን ቁጥር፣ በአውሮፕላን ቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል ብቃት፣ በሰው ኃይል አደረጃጀት፣ በትርፋማነት፣ በሚደርስባቸው መዳረሻዎች ብዛት፣ በሚያገኛቸው ዓለም አቀፍ ሽልማቶች የሚወስደው  “በማለትም ያስረዳሉ ፡፡

ካፒቴን ሰለሞን ግዛው (የአቢሲኒያ የበረራ ድርጅትና የአቪዬሽን አካዳሚ ኃላፊ)በበኩላቸው

"አየር መንገዱ ከዚህ በፊት የነበረው ታሪክ ይሄን ሁሉ ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጎታል። ልማዱ ነው የሚባል አየር መንገድ አይደለም። ምክንያቱም ልምድ ያለው ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ። አሁን ትናትና ተጠይቄ ነበር ካፒቴኑ ወጣት ነው ስምንት ሺህ ሰዓት ብቻ ነው ያለው የሚል እኔም የመለስኩት መልስ ስምንት ሺህ ሰዓት ያለው ሰው ብዙ ጊዜ ውጭ አገር ጡረታ የሚወጣበት ሰዓት ነው" ብለዋል፡፡

አደጋው እጅግ አሳዛኝና ውዱን የሰው ልጆች ህይወት ያሳጣ ቢሆንም አየር መንገዱ የነበረውን መልካም ስምና ተቀባይነት የሚያሳጣው አይሆንም ይላሉበአብራሪነት የካበተ ልምድ ያላቸው የአቢሲኒያ የበረራ ድርጅትና የአቪዬሽን አካዳሚ ኃላፊ ካፒቴን ሰለሞን ግዛው።

የኤሮሪድ አቪዬሽን ሚዲያ ዋና ስራ አስፈጻሚና የግል አውሮፕላን አብራሪ ዮናታን መንክር ካሳም እንዲሁ የምናዝነው ላጣናቸው ነፍሶች እንጂ አየር መንገዱስ የሚገጥመው ኪሳራ አይኖርም ባይ ናቸው።

በወቅቱ አደጋው የደረሰበት አውሮፕላን ላይ መሳፈር የነበረባቸው ሰዎች በተለያየ ምክንያት ሲያመልጣቸው ከአደጋው በኋላም ጉዟቸውን በአየር መንገዱ ቀጣይ በረራ አድርገዋል።

ሌሎች የአየር መንገዱ ደንበኞችም ዛሬም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር መሆናቸውን ለማሳየት ፎቶ ተነስተው በማህበራዊ ድረ-ገጾች በማጋራት አብሮነታቸውን ገልጸዋል።

ከሰሞኑ በአሜሪካ ጋዜጦች ''የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማክስ 8 ምስለ-በረራ (ሲሙሌተር) ቢኖረውም አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን አብራሪ ግን ስልጠናውን አልወሰደም'' በሚል የተሰራጨው ዘገባም ሀሰት መሆኑንና አብራሪዎቹ በቂ ስልጠና ማግኘታቸውን አየር መንገዱ አስታውቋል።

ኒውዮርክ ታይምስና ዋሽንግተን ፖስት ያወጡት ዘገባ የጉዳዩን ዋና ትኩረት ለማሳት የሚደረግ ሙከራ ነው ብሎታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁንም መደበኛ ስራውን እያከናወነ ነው። ወጪ ገቢውም እንደተለመደው እንቅስቃሴ ላይ ነው። ቤቱ ሀዘን ቢገባም ህይወት ቀጥላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም